ብቻ ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ… በማንኛውም መንገድ በተቃዋሚዎቻችሁ አትሸበሩ… በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቶአችኋልና። (ፊልጵስዩስ 1፥27-29)
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ መኖር ማለት፣ በጠላቶች ፊት ያለ ፍርሃት መቆም እንደሆነ ይነግራቸዋል። ከዚያም ያለ ፍርሃት መቆም ምን እንደሆነ ማብራሪያ ይሰጣል።
ማብራሪያው ይህ ነው፦ እግዚአብሔር አንድ ብቻ ሳይሆን ሁለት ስጦታዎች ሰጥቷችኋል፦ እምነት እና መከራ። ቁጥር 29 የሚናገረው ይህንኑ ነው። “በክርስቶስ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን ስለ እርሱ መከራ እንድትቀበሉም ይህ ጸጋ ተሰጥቶአችኋልና።” እንድታምኑ ተሰጥቷችኋል፤ መከራ እንድትቀበሉም ተሰጥቷችኋል።
በዚህ ዐውድ መሠረት፣ በመከራ ውስጥ ያላችሁ እምነት እና መከራችሁ ራሱ የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው። ጳውሎስ በተቃዋሚዎቻችሁ አትሸበሩ ሲል ሁለት ምክንያቶችን ይዞ ነው፦
- አንደኛው ምክንያት፣ ተቃዋሚዎቹ በእግዚአብሔር እጅ ውስጥ መሆናቸው ነው። ተቃውሟቸው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በእርሱ ቁጥጥር ሥር ነው። ይህ የቁጥር 29 የመጀመሪያው ነጥብ ነው።
- ላለመፍራት ሌላው ምክንያት ደግሞ አለመፍራታችን (ማለትም እምነታችን) በእግዚአብሔር እጅ መሆኑ ነው። ይህም ስጦታ ነው። የቁጥር 29 ሌላኛው ነጥብ ይህ ነው።
ስለዚህ በመከራ ውስጥ ያለ ፍርሀት መቆም ሁለት ገጽታ አለው፦ መከራችንም ሆነ፣ በመከራ ጊዜ የሚኖር እምነታችን የእግዚአብሔር ስጦታዎች ናቸው።
ታዲያ ይህ “ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ” መኖር ነው የተባለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ወንጌል የክርስቶስ የቃል ኪዳኑ ደም፣ እምነት እንደሚሰጠን እና ጠላቶቻችንን እንደሚገዛ ያስተምራል። ይህም ወንጌል ሁልጊዜ ለዘላለማዊ ጥቅማችን የሚሆን የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ሥራ እና ለሕዝቡ ሁሉ የሚሆን እንከን አልባ የምሥራች ነው። ወንጌሉ ያረጋገጠው ይህን ነው። ስለዚህ በዚህ መልኩ መኖር የወንጌልን ኃይልና መልካምነት ያሳያል።
በመሆኑም አትፍሩ። ጠላቶቻችሁ እግዚአብሔር ከፈቀደው በላይ ማድረግ አይችሉም። የሚያስፈልጋችሁን እምነት ሁሉ ይሰጣችኋል። እነዚህ ተስፋዎች በደም የተገዙ እና የታተሙ ናቸው። የወንጌል ተስፋዎች ናቸው።