ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው። (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10)
ጸጋ ኃጢአት ስንሠራ የሚደረግልን ምህረት ወይም ማቅለያ ብቻ አይደለም። ጸጋ ኃጢአትን እንዳናደርግ የሚያስችለን የእግዚአብሔር ስጦታ እና ኃይል ጭምር ነው። ይቅርታ ብቻ አይደለም፣ ኃይልም ጭምር ነው።
ለምሳሌ፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10 ላይ ይህ በግልጽ ተቀምጧል። ጳውሎስ ሥራውን እንዲሰራ የሚያስችለው ኃይል ጸጋ እንደሆነ ይናገራል። በጸጋ ያገኘው የኃጢአቱን ይቅርታ ብቻ አይደለም፤ በመታዘዝ ለመቀጠል የሚያስችለውን ኃይልም ጭምር እንጂ። “እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው” ይላል።
ስለዚህ፣ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ የምናደርገው ጥረት በራሳችን ኃይል የሚሆን አይደለም። ይልቁንም፣ “እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት፣ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥11)። ከእምነት የሚመነጭ ታዛዥነት ነው። ማድረግ የሚገባንን ለማድረግ በሚያስችለን፣ በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ በሚመጣው የጸጋ ኃይል ላይ ያለ እምነት ነው።
ጳውሎስ በ2ኛ ተሰሎንቄ 1፥11-12 ላይ፣ እያንዳንዱን የመልካምነት ተግባሮቻችንን “ከእምነት የሆነ ሥራ” ብሎ በመጥራት ይህንን ያረጋግጣል። ከዚያም ይህ ለኢየሱስ የሚሰጠው ክብር “እንደ አምላካችን … ጸጋ መጠን ነው” ምክንያቱም የሚሆነው “በኃይሉ” ነውና በማለት ይናገራል። እያንዳንዱን ሐረግ በሚገባ አድምጡ፦
ይህን እያሰብን አምላካችን ለጥሪው የበቃችሁ አድርጎ እንዲቈጥራችሁ፣ መልካም ለማድረግ ያላችሁን ምኞትና ከእምነት የሆነውን ሥራችሁን ሁሉ በኀይሉ እንዲፈጽምላችሁ ዘወትር ስለ እናንተ እንጸልያለን። ደግሞም እንደ አምላካችንና እንደ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ መጠን የጌታችን የኢየሱስ ስም በእናንተ ዘንድ እንዲከብርና እናንተም በእርሱ እንድትከብሩ ይህን እንጸልያለን።
እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው መታዘዝ የሚመነጨው፣ በእግዚአብሔር የጸጋ ኃይልና በእምነት አማካኝነት ነው። በሁሉም የክርስትና ሕይወት ደረጃዎች ውስጥ ይህ እውነት ይሠራል። በእምነት የሚያድነን የእግዚአብሔር የጸጋ ኃይል፣ ያው ራሱ በእምነት በኩል የሚቀድሰን የእግዚአብሔር የጸጋ ኃይል ነው (ኤፌሶን 2፥8)። ያዳነን ያው ጸጋ በቅድስና እንድንኖር ኀይልን ይሰጠናል።