ጸጋ ነፃ መሆን አለበት | መስከረም 3

ያልተቀበልኸው የራስህ የሆነ ነገር ምን አለ? ከተቀበልህ ታዲያ፣ እንዳልተቀበልህ ለምን ትመካለህ? (1ኛ ቆሮንቶስ 4፥7)

መዳንን እንደምንኖርበት ቤት አድርገን እናስብ።

ጥበቃ ይሰጠናል። ለዘላለም የሚቆይ ምግብና መጠጥ ሞልቶበታል። መቼም አይፈርስም። ፍጹም የሚያረካ ክብር የሚታይባቸው መስኮቶች ሁሌም እንደተከፈቱ ናቸው።

እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሳይሰስት በመስጠት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎበታል፤ ለእኛም በነፃ ሰጥቶናል።

“የግዢ” ስምምነቱ “አዲሱ ኪዳን” ይባላል። ስምምነቱም እንዲህ ነው፦ “ይህ ቤት የእናንተ ሊሆን የሚችለው እንደ ስጦታ ስትቀበሉት እና ደስታችሁ በዚህ ቤት ውስጥ በሚኖሩት በአብና በወልድ ላይ ብቻ ሲሆን ነው። ሌሎች አማልክትን በማስጠለል የእግዚአብሔርን ቤት አታርክሱ፤ ልባችሁንም ወደ ሌላ ሀብት አታዙሩ፤ ነገር ግን እዚህ ቤት ባለው በእግዚአብሔር ኅብረት እርካታን አግኙ“ የሚል ነው።

ለዚህ ስምምነት አዎንታዊ ምላሽ ከሰጡ በኋላ፣ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ክፍያውን በራሴ አቅም እከፍላለሁ በሚል ተስፋ ጠበቃ ቀጥሮ፣ የወርሃዊ ክፍያ ዕቅድ አውጥቶ፣ የብድር ማስታገሻ መንገድን መፈለግ ሞኝነት አይሆንም?

ይህን ማድረግ ቤቱን እንደ ስጦታ ሳይሆን እንደ ግዢ መቁጠር ይሆናል። እንዲያ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ቸር አይሆንም። ከዚህም ባለፈ እርሱ በእናንተ ላይ ፈጽሞ ሊጭን ላላሰበው ቀንበር ባሪያ ትሆናላችሁ።

ጸጋን ጸጋ ያስባለው ነፃ መሆኑ እስከሆነ ድረስ፣ በክፍያ እንደሚገኝ ወይም መልሰን ልንከፍለው እንደሚገባ ዕዳ ልንቆጥረው አይገባም።