እግዚአብሔር ሆይ ምሕረት አድርግልኝ | ነሐሴ 10

እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ (መዝሙር 51፥1)።

ዘማሪው በዚህ ቦታ እየደጋገመ “እንደ ቸርነትህ መጠን” እና “እንደ ርኅራኄህም ብዛት” “ምሕረት አድርግልኝ” ይላል።

በዘጸአት 34፥6-7 ላይ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠው ይህንን ነው፦

“እግዚአብሔር ሩኅሩኅ ቸር አምላክ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ፣ ፍቅርን ለሺዎች የሚጠብቅ፣ ክፋትን፣ ዐመፅንና ኀጢአትን ይቅር የሚል በደለኛውን ግን ሳይቀጣ ዝም ብሎ አይተውም፤ በአባቶች ኀጢአት ልጆችን የልጅ ልጆቻቸውን እስከ ሦስትና አራት ትውልድ ይቀጣል።”

ይቅር የማይባሉ በደለኞች እንዳሉ ዳዊት ያውቃል። ደግሞም በደለኞች ሆነው ተዓምራዊ በሆነ የመቤዠት ሥራ እንደ በደለኛ መቆጠራቸው ቀርቶ ይቅር የሚባሉ መኖራቸውንም ያውቃል። በዚህም መዝሙር ላይ ዳዊት ይህንን ታዓምራዊ የሆነ ምሕረት ሲደገፍበት እንመለከታለን።

“እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ መጠን፣ ምሕረት አድርግልኝ፤ እንደ ርኅራኄህም ብዛት፣ መተላለፌን ደምስስ” ይላል። የዚህን የመቤዠት ተዐምር ከዳዊት በበለጠ እኛ እናቀዋለን። ምክንያቱም ክርስቶስን እናውቃለን። ከዚያ ግን ዳዊት ምሕረቱን እንደተደገፈ እንዲሁ እኛም ምሕረቱ ላይ እንደገፋለን።

ዳዊት ያደረገው ወሳኝ ነገር፣ ከነድካሙ እርዳታን በመሻት ወደ እግዚአብሔር ምሕረት እና ፍቅር መዞሩ ነው። ይህ ማለት፣ ዛሬ ላይ ላለን ለእኛ፣ ከነድካማችን እርዳታን ፍለጋ ወደ ከርስቶስ መዞር ማለት ነው፤ በፈሰሰው ደሙ አማካኝነት የሚያስፈልገንን ምሕረት ሁሉ ልናገኝ እንችላለን።