ሞትን መለማመድ | ጳጉሜ 5

እንደ ጐርፍ ጠርገህ ስትወስዳቸው፣ እንደ ሕልም ይበንናሉ፤ እንደ ማለዳ ሣር ታድሰው ይበቅላሉ፤ ሣሩም ንጋት ላይ አቈጥቍጦ ይለመልማል፤ ምሽት ላይ ጠውልጎ ይደርቃል። ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቍጠር አስተምረን” (መዝሙር 90፥5-6፣ 12)

ለእኔ የዓመት መጨረሻ እንደ ሕይወቴ መጨረሻ ነው። የዓመቱ የመጨረሻ ቀን፣ የመጨረሻ ሰዓት የሆነው ጳጉሜ 5 ከምሽቱ 11፡59 ሲል፣ ልክ እንደ ሞቴ ቅጽበት እቆጥረዋለሁ።

የዓመቱን 365 ቀናት እንደ አንድ የህይወት ዘመን ናሙና እመለከታቸዋለሁ። የዓመቱን የመጨረሻ ቀን ደግሞ የምመለከተው ልክ ዶክተሩ መጨረሻው በጣም እንደቀረበ ከነገረኝ በኋላ በሆስፒታሉ ውስጥ እንዳሉኝ የመጨረሻዎቹ ቀናት ነው። በእነዚህ የመጨረሻ ሰዓታት ውስጥ፣ የዚህ ዓመት የህይወት ዘመን በዓይኔ ፊት ያልፋል፤ እናም አንድ የማይቀር ጥያቄ እጋፈጣለሁ፤ ይህን ሕይወት በሚገባ ኖሬዋለሁ? ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ “ደግ አድርገሃል፤ አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ” ይለኝ ይሆን (ማቴዎስ 25፥21)?

ዓመቴን የምጨርሰው በዚህ መንገድ በመሆኑ በጣም እድለኛ ነኝ። ለእናንተም የዓመቱ መጨረሻ ተመሳሳይ ትርጉም እንዲኖረው እጸልያለሁ።

እድለኛ እንደሆንኩ የሚሰማኝ ሞቴን መለማመዴ ትልቅ ጥቅም አለው ብዬ ስለማስብ ነው። ለሕይወታችን የመጨረሻው ትዕይንት ለመዘጋጀት በዓመት አንድ ጊዜ መለማመዱ ፋይዳው ቀላል አይደለም። ምክንያቱም መስከረም 1 ማለዳ አብዛኞቻችን በህይወት እንነቃለን፤ በአዲስ የህይወት ዘመን አፋፍ ላይ፣ እንደገና እንደ አዲስ መጀመር እንችላለን።

እንዲህ ያለው ልምምድ ትልቁ ጥቅም ድክመቶቻችን የት እንዳሉና ያልተዘጋጀንባቸው ነገሮች ምን ምን እንደሆኑ ፍንትው አድርጎ ስለሚያሳየን ነው። በዋናው የግጥሚያ ዕለት በትክክለኛ ተመልካቾች ፊት እውነተኛውን ፍልሚያ ከመፋለማችን በፊት ለመለወጥ፣ ለማደግና ለመሻሻል ጊዜ ይሰጠናል።

ለአንዳንዶቻችሁ ስለሞት ማሰብ በጣም ከባድ ነው። አስፈሪ፣ አደንዛዥ፣ ጭልምልም ያለ፣ በሀዘንና በጭንቀት የተሞላ በመሆኑ በተለይ በበዓላት ወቅት ከአእምሯችሁ ለማስወጣት የተቻላችሁን ጥረት ታደርጋላችሁ። ይህ ግን ልክ አይመስለኝም። ስለ ሞት በጥበብ ማሰብ ይቻላል። ማሰቡ ደግሞ ጠቀሜታ አለው። በሕይወቴ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ ሃሳቦች መካከል ስለ ራሴ ሞት በየሆነ ጊዜ ማሰብ ነው።

ምርጡን ኑሮ መኖር የሚቻልበትን ዘዴ ለማወቅ የሚያስችለውን ጠቢብ ልብ እንዴት ታገኛለህ? ዘማሪው እንዲህ ይመልሳል፦ 

“እንደ ጐርፍ ጠርገህ ስትወስዳቸው፣ እንደ ሕልም ይበንናሉ፤ እንደ ማለዳ ሣር ታድሰው ይበቅላሉ፤ ሣሩም ንጋት ላይ አቈጥቍጦ ይለመልማል፤ ምሽት ላይ ጠውልጎ ይደርቃል….. ጥበብን የተሞላ ልብ ይኖረን ዘንድ፣ ዕድሜያችንን መቍጠር አስተምረን።” (መዝ 90:5-6፣ 12)

ዕድሜን መቁጠር ማለት ህይወታችን አጭር እንደሆነ እና ሞታችን በቅርቡ እንደሚሆን ማስታወስ ማለት ነው። የሕይወትን አቅጣጫ የሚለውጥ ታላቅ ጥበብ የሚገኘው እነዚህን ነገሮች በየጊዜው በማሰላሰል ውስጥ ነው።

ጳውሎስ ሕይወቱን ለመለካት የተጠቀመበት የስኬት መስፈርት፣ “እምነቴን ጠብቄ ነበር ወይ?” የሚል ነው። “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤
ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፥ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ ያን ቀን ለእኔ ያስረክባል፥ ደግሞም መገለጡን ለሚወዱት ሁሉ እንጂ ለእኔ ብቻ አይደለም።” (2 ጢሞ 4:7-8)። ይህ በየዓመቱ ማለቂያ ሕይወታችንን የምንለካበት ቱንቢና የምንመዝንበት ሚዛናችን ይሁንልን።

በዚህ በሚያልፈው ዓመት በእምነታችን እንዳልጠነከርን ወይም ማደግ ያለብንን ያክል እንዳላደግን ከተገነዘብን ደስ ሊለን ይገባል፤ ምክንያቱም ይህ አመት የመጨረሻው ሞት ልምምድ ብቻ ነው። ማንቂያ ደውላችን ነው። ከነገ ጀምሮ እምነታችንን በመፍራትና በመንቀጥቀጥ ለመፈጸም የምንችልበት ሙሉ ህይወት ከፊታችን አለ። ይህ አዲሱ ዓመት፣ እግዚአብሔርን የበለጠ የምናውቅበት፣ የምንወድድበትና የምንመስልበት ዓመት ይሁንልን!