ስለዚህ፣ ‘ምን እንበላለን? ምን እንጠጣለን? ምንስ እንለብሳለን?’ ብላችሁ አትጨነቁ፤ አሕዛብ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ለማግኘት ይጨነቃሉና፤ የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል። (ማቴዎስ 6፥31-32)
ኢየሱስ ተከታዮቹ ከጭንቀት ነጻ እንዲሆኑ ይፈልጋል። በማቴዎስ 6፥25-34 ላይ ጭንቀታችንን ከእኛ ሊወስዱ የሚችሉን ቢያንስ ሰባት መንገዶችን ይናገራል። አንደኛው ስለ ምግብ፣ መጠጥና ልብስ አንስቶ፣ “የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” ይለናል (ማቴዎስ 6፥32)።
ኢየሱስ “እግዚአብሔር ያውቃል” ሲል፣ “እነዚህን ነገሮች ሊያሟላልን ይፈልጋል” ማለቱም ጭምር መሆን አለበት። አባት እንዳለን እያስረገጠልን ነው። ይህም አባት ከማንኛውም ምድራዊ አባት የተሻለ ነው።
አምስት ልጆች አሉኝ። ፍላጎታቸውን ማሟላት ያስደስተኛል። የእኔ ማወቅ ግን ከእግዚአብሔር ማወቅ በሶስት መንገዶች ያንሳል።
አንደኛ፣ አሁን ልጆቼ የት እንዳሉ አላውቅም። ልገምት ችላለሁ፤ በደህንነት ተጠብቀው ቤታቸው ወይም ስራ ቦታ ወይም ትምህርት ቤት ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን መንገድ ዳር ታመው ወድቀው ሊሆንም ይችላል።
ሁለተኛ፣ በየትኛውም ሰዓት ልባቸው ውስጥ ያለውን ማወቅ አልችልም። አንዳንዴ ልገምት እችላለሁ። ነገር ግን ፍርሃት ወይም ቁጣ ወይም ሀዘን ወይም ክፉ ምኞት ወይም ደስታ ወይም ተስፋ እየተሰማቸው ሊሆን ይችላል። የልባቸውን ማየት አልችልም። እንኳን እኔ፣ እነርሱ ራሳቸው ሙሉ ለሙሉ በልባቸው ያለውን አያውቁም።
ሶስተኛ፣ የወደፊታቸውን አላውቅም። አሁን ደህና ደግሞም የተረጋጉ ሊመስሉ ይችላሉ። ነገር ግን ነገ ከባድ ሀዘን ሊመጣባቸው ይችላል።
ይህ ማለት እንዳይጨነቁ በቂ ምክንያት ልሆንላቸው አልችልም ማለት ነው። አሁን ላይ እየሆነባቸው ያለ እኔ ማላውቀው፣ ወይም ነገ ላይ የሚሆንባቸው ነገር ሊኖር ይችላል። በሰማይ ላለው አባታቸው ግን ፈጽሞ የተለየ ነው። በሰማይ ያለው አባታችን ሁሉ ነገራችንን ያውቃል። ማንነታችንን፣ ዛሬንና ነገን፣ ሁለንተናችንን ያውቃል። የሚያስፈልንን ሁሉ ይመለከታል።
ከዚያ በተጨማሪ ደግሞ፣ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሁሉ ሊያሟላልን አጥብቆ ይፈልጋል። በማቴዎስ 6፥30 ላይ “አብልጦ” የሚለውን አስታውሱ። “እግዚአብሔር ዛሬ ታይቶ በነጋታው እሳት ውስጥ የሚጣለውን የሜዳ ሣር ይህን ያህል ካለበሰ እናንተንማ እንዴት አብልጦ አያለብሳችሁ?”
ከዚህም በተጨማሪ፣ ሊያደርገው አጥብቆ የሚፈልገውን ነገር ለማድረግ ሙሉ አቅም አለው። በዓለም ላይ ያሉትን በቢልዮን የሚቆጠሩ አእዋፋትን ያለማቋረጥ ይመግባል (ማቴዎስ 6፥26)።
ስለዚህ ኢየሱስ የሚያስፈልገንን ሊሰጠን የገባውን ቃል አብራችሁኝ እመኑ። “የሰማዩ አባታችሁም እነዚህ ሁሉ ለእናንተ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል” ሲለን ወደዚህ እምነት እየጠራን ነው።