በሚመጣው ቁጣ የሰማይ እፎይታ | ሐምሌ 2

እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤ መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል። ይህም የሚሆነው ጌታ ኢየሱስ በሚንበለበል እሳት ከኀያላን መላእክት ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ነው። በዚያ ጊዜ እግዚአብሔርን የማያውቁትንና ለጌታችንም ለኢየሱስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል። (2ኛ ተሰሎንቄ 1፥6–8)

የእግዚአብሔር ትዕግስት የሚያበቃበት ጊዜ ይመጣል። እግዚአብሔር ሕዝቡ የተመደበላቸው ጊዜ እስኪያበቃ እና የተወሰነውም የሰማዕታት ቁጥር እስኪሞላ የልጆቹን መሰቃየት ዝም ይላል። ያ ጊዜ ሲያበቃ ግን ቅዱስና ጻድቅ የሆነ በቀል ከሰማይ ይወርዳል (ራእይ 6፡11)።

ሕዝቡን ባስጨንቁት ሰዎች ላይ እግዚአብሔር የሚወስደው የበቀል እርምጃ፣ በእኛ ዘንድ እንደ “ዕረፍት” መሆኑን አስተውሉ። “እግዚአብሔር ጻድቅ በመሆኑ መከራን ለሚያመጡባችሁ መከራን ይከፍላቸዋል፤ መከራን ለተቀበላችሁት ለእናንተም ሆነ ለእኛ ደግሞ ዕረፍት ይሰጠናል።” በሌላ አነጋገር፣ “መከራ በሚያመጡብን ሰዎች” ላይ ያለው ፍርድ ለእኛ እንደ አንድ የጸጋ ዓይነት ነው።  

ፍርድን እንደ ጸጋ ሊያሳየን የሚችል እጅግ አስደናቂ የሆነ ሥዕል ያለው ምናልባትም በዮሐንስ ራእይ 18 ላይ ስለባቢሎን መጥፋት ሲናገር ነው። በውድመቷ ጊዜ ታላቅ ድምፅ ከሰማይ እንዲህ ሲል ጮኸ፡- “ሰማይ ሆይ፤ በእርሷ ላይ ሐሤት አድርግ! ቅዱሳን፣ ሐዋርያትና ነቢያትም ሐሤት አድርጉ! በእናንተ ላይ ባደረሰችው ነገር እግዚአብሔር ፈርዶባታልና” (ራእይ 18:20)። ያን ጊዜ ብዙ ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ይሰማል፦ “ሃሌ ሉያ! ማዳን፣ ክብርና ኀይል የአምላካችን ነው፤ ፍርዱ እውነትና ጽድቅ ነውና፤ በዝሙቷ ምድርን ያረከሰችውን፣ ታላቂቱን አመንዝራ ፈርዶባታል፤ ስለ አገልጋዮቹም ደም ተበቅሏታል” (ራእይ 19፡1-2)።

ይህ የምሕረት ዘመን አብቅቶ የእግዚአብሔር ትዕግሥትና የበዛ ታጋሽነቱ ሲያልፍ፣ ጽዋውም ሲሞላ እና በእግዚአብሔር ሕዝብ ጠላቶች ላይ ፍርድ ሲመጣ፣ ቅዱሳን የአምላካቸውን ፍትህ አይቃወሙም፣ የድርጊቱንም ትክክለኝነት ያውጃሉ።

ይህ ማለት ንስሓ የማይገቡ ሰዎች የመጨረሻ ጥፋት፣ ለእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ መከራ ሆኖ አይሰማቸውም ማለት ነው።

የሌሎች ንስሓ ለመግባት ፈቃደኛ አለመሆን የቅዱሳንን ፍቅር አይከለክልም፣ አያግትም። ሲኦል መንግሥተ ሰማይን ሊያስፈራራና ሊያስጨንቅ ከቶ አይቻለውም። የእግዚአብሔር ፍርድ ይፀድቃል፣ ትክክለኝነቱም ይታወጃል። የእውነትና ጽድቅ ትክክለኝነት መታወጁ፣ ለጻድቃን ታላቅ ጸጋ ይሆንላቸዋል።