እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ። (ሮሜ 12፥3)
በዚህ ክፍል አውድ ላይ፣ ጳውሎስ፣ ሰዎች ‘ከሆኑት በላይ ራሳቸውን ከፍ አድርገው’ ማየታቸው እንዳሰሰበው እንመለከታለን። ለዚህም ትዕቢት የመጨረሻ መድኃኒት ያደረገው፣ መንፈሳዊ ስጦታዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ እነዚያን ስጦታዎች የምንጠቀምበት እምነትም ጭምር፣ በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔር የነጻ ጸጋ ሥራ መሆኑን መናገርን ነው። “. . . ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን” ይላል።
ይህ ማለት ልንመካ የምንችልባቸው ምክንያቶች ሁሉ ከእኛ ተወስደዋል ማለት ነው። ስጦታዎችን ለመቀበል ብቁ ያደረገን ሌላ ስጦታ ከሆነ እንዴት መመካት እንችላለን?
ይህ እውነት ጸሎታችን ላይ መሰረታዊ ተጽዕኖ አለው። ኢየሱስ በሉቃስ 22፥31-32 ላይ የዚህን ምሳሌ ይሰጠናል። ጴጥሮስ ሦስት ጊዜ ከመካዱ በፊት ኢየሱስ እንዲህ ይለዋል፡- “ስምዖን ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፤ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።”
ኢየሱስ እምነትን የሚሰጠው እግዚአብሔር መሆኑን ስለሚያውቅ፣ በክህደት ኃጢአት ውስጥ እንኳ እያለ የጴጥሮስን እምነት እግዚአብሔር እንዲያጸና ይጸልይለታል። ስለዚህ፣ እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር የራሳችንንም ሆነ የሌሎችንም እምነት እንዲያጸና መጸለይ አለብን።
ልክ እንዲሁ፣ በሚጥል በሽታ የሚሰቃይ ልጅ የነበረው ሰው፣ “አምናለሁ፤ አለማመኔን ርዳው!” ብሎ ጮዃል (ማርቆስ 9፥24)። ይህ እጅግ መልካም የሆነ ጸሎት ነው። ከእግዚአብሔር እርዳታ ውጪ የሚገባንን ያህል ማመን እንደማንችል እውቅናን የሚሰጥ ጸሎት ነው።
ስለዚህ ይህንን ጸሎት በየዕለቱ እንጸልይ፦ “ጌታ ሆይ፣ ስለ እምነቴ አመሰግንሃለሁ። እምነቴን አፅና። አጠንክረው። ሥር እንዲሰድድ አድርገው። እንዲጠፋ አትፍቀድለት። አንተ እንደ ታላቅ ሰጪነትህ ክብርን ሁሉ ትወስድ ዘንድ፣ በማደርገው ነገር ሁሉ እምነቴን የሕይወቴ ኃይል አድርገው። ጌታ ሆይ አንተ ላይ ያለኝን እምነት አብዛልኝ! አሜን።”