የእርሱ ጊዜ ፍጹም ነው | ሐምሌ 18

እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም [በትክክለኛውም] ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ። (ዕብራውያን 4፥16)

ይህ የከበረ ጥቅስ በተለምዶ የሚተረጎመው “ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ በእምነት ወደ ጸጋው ዙፋን እንቅረብ” ተብሎ እንደሆነ አውቃለሁ። በዚህ መንገድ ተጠጋግቶ የተተረጎመው እግዚአብሔር በምንፈልገው ጊዜ እንደሚገለጥ ለማሳየት ሲባል ነው። እውነትም ነው። ነገር ግን የቀጥተኛው ትርጉም ዋናው ትኩረት እርዳታው ምን ያህል በትክክለኛ ጊዜ ላይ መሰጠቱን ማመልከት ነው።

አገልግሎቶች ሁሉ የሚፈጸሙት ወደፊት ነው። ወይ ከደቂቃዎች በኋላ፣ ወይም ከወራት፣ አልያም ከዓመትና ከዐሥርት ዓመታት በኋላ ነው። ሁሌም ቢሆን ድካማችንን በርትቶ ለአገልግሎት ብቁ ባለመሆናችን ልናዝን እንችላለን፤ ይህ ሲሆን ደግሞ በጸሎት ልንተጋ ይገባል።

ጸሎት ማለት ለነገ አገልግሎት ብቁ ከሚያደርገን ጸጋ ጋር ዛሬ ላይ የሚያገናኘን አንዱ የእምነት መንገድ ነው። ሁሉም ነገር በትክክለኛው ጊዜ መደረጉ እጅግ ወሳኝ ነው።

ጸጋው ቀድሞ ወይም በጣም ዘግይቶ ቢመጣስ? የዕብራውያን 4፥16 የድሮ ትርጉም ከዚህ አንጻር በጣም ውድ የሆነውን ተስፋ ግልጽ አያደርግም። ግልጽ እንዲሆን በቀጥታ መተርጎም ይኖርበታል። ተስፋው “በሚያስፈልገን ጊዜ የሚረዳን” ጸጋ ማግኘታችን ብቻ ሳይሆን ጸጋው በትክክለኛው ጊዜ በእግዚአብሔር  የተሰጠን መሆኑ ነው።

ዋናው ነጥብ፣ ጸሎት በትክክለኛው ጊዜ ለሚሆን እርዳታ የእግዚአብሔርን ጸጋ የምናገኝበት መንገድ ነው የሚል ነው። ይህ የእግዚአብሔር ጸጋ ሁልጊዜ “ከጸጋው ዙፋን” በትክክለኛው ጊዜ ይደርሳል። “የጸጋ ዙፋን” የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው የወደፊቱ ጸጋ የሚመጣው፣ በሥልጣኑ ጊዜን ከሚወስነው ከአጽናፈ ዓለሙ ንጉሥ መሆኑን ነው (ሐዋሪያት ሥራ 1፥7)።

የእርሱ ጊዜ ፍጹም ነው፤ የእኛ ጊዜ ግን የእኛ ራሱ አይደለም። “ሺህ ዓመት በፊትህ፣ እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን፣ እንደ ሌሊትም እርቦ ነውና” (መዝሙር 90፥4)። በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ መንግሥታት የሚነሡበትን እና የሚወድቁበትን ጊዜ የሚወስነው እርሱ ነው (ሐዋሪያት ሥራ 17፥26)። በግለሰብ ደረጃ ደግሞ፣ የእያንዳንዳችን ዘመን ያለው በእጁ ነው (መዝሙር 31፥15)።

የወደፊቱ ጸጋ ስለሚገለጥበት ሰዓት ትክክለኝነት ስንጨነቅ፣ ስለ “ጸጋው ዙፋን” ማሰብ አለብን። እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ጸጋ በትክክለኛው ጊዜ ለመስጠት ያቀደውን ዕቅድ ምንም ነገር ሊያደናቅፍበት አይችልም። የወደፊቱ ጸጋ ሁሌም በትክክለኛው ጊዜ የሚመጣ ነው።