ተስፋችሁን አጥብቃችሁ ያዙ | ሕዳር 17

እግዚአብሔር የማይለወጥ ዐላማውን ለተስፋው ቃል ወራሾች ግልጽ ለማድረግ ስለ ፈለገ፣ በመሐላ አጸናው፤ እግዚአብሔር ከቶ ሊዋሽ አይችልም፤ እርሱ በሁለት በማይለወጡ ነገሮች በፊታችን ያለውን ተስፋ ለመያዝ ወደ እርሱ ለሸሸን ለእኛ ብርቱ መጽናናት እንድናገኝ አድርጎአል። (ዕብራውያን 6፥17–18)

የዕብራውያን ጸሐፊ ተስፋችንን አጥብቀን እንድንይዝ የሚያበረታታን ለምንድን ነው? የተስፋችን የመጨረሻ ደስታ በኢየሱስ ደም የተገኘና የማይሻር ከሆነ፣ ታዲያ እግዚአብሔርን አጥብቀን እንድንይዝ ለምን ነገረን?

መልሱ ይህ ነው፦ 

  • ክርስቶስ በሞቱ አማካኝነት አጥብቀን መያዝ የሚያስችለንን ኃይል ገዛልን እንጂ፣ አጥብቀን ከመያዝ ነጻ አላወጣንም።
  • እርሱ ሞቷልና ከእንግዲህ ፍቃዳችን ምንም ሚና የለውም፣ አጥብቀን መያዝም አያስፈልገንም ማለት አይደለም። ይልቅ አጥብቀን የመያዝ ፍላጎት እንዲኖረን ፍቃዳችንን በኅይሉ አስታጥቆ ለውጦታል።
  • ክርስቶስ በመስቀሉ ስራ መዳናችንን አጥብቀን እንድንይዝ የታዘዝነውን ትዕዛዝ ፈጸመው እንጂ አልሻረውም።
  • ክርስቶስ በመስቀሉ ስራ የቃሉን ምክር እና ተግሳጽ ድል እንዲነሳ አደረገው እንጂ አልሻረውም።

ክርስቶስ የሞተው፣ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 3፥12 ላይ ያደረገውን እናንተም እንድታደርጉ ነው። “ክርስቶስ ኢየሱስ እኔን የራሱ ያደረገበትን ያን፣ እኔም የራሴ ለማድረግ እጣጣራለሁ”። ለአንድ ኅጢአተኛ በእግዚአብሔር ተስፋ ማድረግ የሚችልበትን ብቸኛ አቅም የሚያገኘው ከክርስቶስ ብቻ እንደሆነ መናገር ሞኝነት ሳይሆን ወንጌል ነው።

ስለዚህም በፍጹም ልቤ እመክራችኋለሁ፤ ክርስቶስ እናንተን የያዘበትን ያን ተዘርግታችሁ ያዙ። ባላችሁ ኃይል ሁሉ አጥብቃችሁ ያዙት፤ ኅይላችሁ ሁሉ የሚገኘው ከእርሱ ኃይል ነው። መታዘዛችሁ በደሙ የተገዛ ስጦታ ነው።