ፍጹማን ላልሆኑ ክርስቲያኖች ተስፋ | ጥር 4

በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል። (ዕብራውያን 10፥14)

ይህ ጥቅስ እንደ እኛ ፍጹማን ያልሆኑ ኃጢአተኞችን የሚያበረታታ እና ለቅድስና የሚያሳሳ ነው።

ይህ ማለት በሰማያዊ አባታችሁ ፊት ፍጹም ሆናችሁ መቆማችሁን ማረጋገጥ ትችላላችሁ፤ ይህም አሁን ፍጹማን ስለሆናችሁ ሳይሆን በእርግጥ አሁን ፍጹማን ስላልሆናችሁ፣ ነገር ግን “ስለምትቀደሱ” እና “ፍጹማን ስለምትሆኑ” ማለት ነው፤ በእግዚአብሔር ተስፋዎች ላይ በማመን ከጉድለቶቻችሁ እየራቃችሁ ወደ ቅድስና የበለጠ እየሄዳችሁ ስለሆነ ማለት ነው። የዕብራውያን 10፥14 ዋና ሐሳብ ይህ ነው።

እምነታችሁ ኃጢአትን እንድትተዉና በቅድስና እንድታደርጉ እያደረጋችሁ ነው? በፍጽምና ጉድለት መካከል ሆኖ ወደ ክርስቶስ በመመልከት “በፊትህ ፍጹም አድርገኸኛል” የሚለው እምነት እንዲህ ያለው ነው።

ይህ እምነት እንዲህ የሚያስብለን ነው፦ “ክርስቶስ ሆይ፣ ዛሬ በድያለሁ። እኔ ግን ኃጢአቴን እጠላለሁ። ሕግን በልቤ ጽፈሃልና፣ ላደርገውም እናፍቃለሁ። በፊትህ ደስ የሚያሰኘውን በእኔ እያደረክ ነው (ዕብራውያን 13፥21)። ስለዚህ፣ የማደርገውን ኃጢአት እጠላዋለሁ፣ የማስባቸውንም የኃጢአት ሐሳቦች እጠላቸዋለሁ።”

ይህ የሚያድነው እውነተኛው እምነት ነው። “በአንዱ መሥዋዕት እነዚያን የሚቀደሱትን ለዘላለም ፍጹማን አድርጎአቸዋል” የሚሉትን ቃላት ማጣጣም የሚችለው እምነት ይህ ነው። ይህ የጠንካሮች ትምክህት አይደለም። አዳኝ የሚያስፈልጋቸው የደካሞች ጩኸት ነው።

በዚህ መንገድ ክርስቶስን ለማመን ደካሞች እንድትሆኑ እጋብዛችኋለሁ፣ ደግሞም እለምናችኋለሁ።