ለምምረው ምሕረት አደርጋለሁ፤ ለምራራለትም ርኅራኄ አደርጋለሁ። (ዘፀአት 33፥19)
ሙሴ ጣዖት ላመለኩት እና ከግብፅ ባርነት የታደጋቸውን አምላክ ለናቁት አንገተ ደንዳና ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ምሕረት ያደርግላቸው እንደሆነ ተስፋ አስፈልጎት ነበር።
እግዚአብሔር ሙሴ የሚፈልገውን ተስፋ እና እርግጠኛነት ለመስጠት፣ “ለምራራለት ርኅራኄ አደርጋለሁ” ብሏል። በሌላ አነጋገር፣ “የእኔ ምርጫዎች በሰው ውስጥ ባለው የክፋት ወይም የመልካምነት ደረጃ ላይ የተመሠረቱ አይደሉም፤ ነገር ግን በእኔ ነፃ ሉዓላዊ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረቱ ናቸው። ስለዚህ ጸጋ ሊያድነው የማይችል እጅግ ክፉ ሰው የለም።” እንዲያ ካልሆነ እግዚአብሔር ነፃ አይደለም ማለት ነው፤ ምርጫም ያለ ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ያበቃል።
ያለ ቅድመ ሁኔታ የመመረጥ አስተምህሮ፣ ከኃጢአተኞች እጅግ ለከፉት የሚሆን ታላቅ የተስፋ ትምህርት ነው። ይህ ማለት ጸጋን ለመቀበል እጩ ለመሆን፣ የእኛ ሁኔታ ከእግዚአብሔር ምርጫ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ይሄ መልካም ዜና ነው።
ዳግመኛ ካልተወለዳችሁ እና በኢየሱስ ክርስቶስ ወደሚያድነው እምነት ካልመጣችሁ፣ ይህን አስቡ፦ የቀድሞው ሕይወታችሁ እጅግ በክፋት የተሞላ ወይም በእግዚአብሔር የጸጋ ሥራ ፈጽሞ የማይናድ ተራራ እንደሆነ በማሰብ በተስፋ መቁረጥ አትመላለሱ። እግዚአብሔር ከኃጢአተኞች እጅግ የከፋውን በማዳን፣ የጸጋውን ነፃነት ማጉላት ይወዳል።
ከኃጢአታችሁ ተመለሱ፤ ጌታንም ጥሩት። ይህን የዕለት ጥሞና በምታነቡበት ወይም በምትሰሙበት ጊዜ፣ እየራራላችሁ እና ወደ እርሱ ምሕረት ዘንበል እንድትሉ ጠንካራ ማበረታቻ እየሰጣችሁ ነው።
“’ኑና እንዋቀስ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘ኀጢአታችሁ እንደ ዐለላ ቢቀላ እንደ በረዶ ይነጣል፤ እንደ ደም ቢቀላም እንደ ባዘቶ ነጭ ይሆናል’” (ኢሳይያስ 1፥18)።