ከባባድ ትእዛዛትን ለመታዘዝ የሚሆን ተስፋ | ነሐሴ 18

ሕይወትን የሚወድ፣ መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ … ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ።” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥10-11)

የጌታ ኢየሱስን ትእዛዛት የማንታዘዝበት መሠረታዊ ምክንያት፣ መታዘዝ ካለመታዘዝ የበለጠ በረከትን እንደሚያመጣልን ከልብ የሆነ መተማመን ስለሌለን ነው። እግዚአብሔር በሰጠን ቃልኪዳን ላይ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አናደርግም። ስለዚህም እንዝላለን።

ምንድነው ይህ የሰጠው ተስፋ? ጴጥሮስ የጌታ ኢየሱስን ተስፋ በዚህ መልኩ ይገልጸዋል፦

ክፉን በክፉ ወይም ስድብን በስድብ ፈንታ አትመልሱ፤ በዚህ ፈንታ ባርኩ፤ ምክንያቱም እናንተ የተጠራችሁት እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች እያደረጋችሁ በረከትን ለመውረስ ነው። ስለዚህ፣ “ሕይወትን የሚወድ፣ መልካም ቀኖችን ሊያይ የሚፈልግ፣ . . . ከክፉ ይራቅ፤ መልካምንም ያድርግ” (1ኛ ጴጥሮስ 3፥9-11)።

ጴጥሮስ ከባድ የሆኑ ትእዛዛትን ታዘዙ ብሎ ለማበረታታት አያፍርም። ይህንንም የሚያደርገው የኢየሱስን ፈለግ በመከተል፣ በመታዘዝ ውስጥ ቃል የተገባልንን የላቀ እና ዘላቂ ደስታ በማስታወስ ነው። ለምሳሌ፣ ክፉን በክፉ አለመመለስ።  “በረከትን ለመውረስ በስድብ ፈንታ ባርኩ” ይለናል። በዘላለም ሕይወት መደሰት ትፈልጋላችሁ? ከክፋት ራቁ! የዘላለም ደስታ ይጠብቃችኋል! ታዲያ ይህ ተስፋ አሁን በመበቀል የሚገኘውን እርካታ ንቆ ለመተው የሚያስችል ብድራት አይደለምን?

መታዘዛችሁ ሕይወታችሁን ቢያሳጣችሁ እንኳ ካለመታዘዝ ሁልጊዜ ኢየሱስን መታዘዝ እጅግ የተሻለ ነው። ኢየሱስ ያለውን አስታውሱ፦

“እውነት እላችኋለሁ፤ ስለ እኔና ስለ ወንጌል ሲል ቤቱን ወይም ወንድሞቹን ወይም እኅቶቹን ወይም እናቱን ወይም አባቱን ወይም ልጆቹን ወይም ዕርሻውን የተወ ሁሉ፣ … መቶ ዕጥፍ የማይቀበል፣ በሚመጣውም ዓለም የዘላለም ሕይወት የማይወርስ የለም” (ማርቆስ 10፥29-30)።

ዋጋን በሚያስከፍለው የፍቅር መንገድ ክርስቶስን ለመከተል ኀይል የምናገኘው ይህንን ተስፋ አጥብቀን ስንይዝ ብቻ ነው። ይህም ተስፋ ፈቃዱን በማድረግ ውስጥ ሕይወታችንን ብናጣ እንኳ ዳግም እንደምናገኘውና ለዘላለምም ብዙ ብድራትን እንደምንወረስ ያረጋግጥልናል።