ሙታንን፣ ታላላቆችንና ታናናሾችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፤ መጻሕፍትም ተከፈቱ። ሌላም መጽሐፍ፣ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ተከፈተ፤ ሙታንም በመጻሕፍቱ ተጽፎ በተገኘው መሠረት እንደ ሥራቸው መጠን ተፈረደባቸው። (ራእይ 20፥12)
የመጨረሻው ፍርድ እንዴት ነው የሚሆነው? ኃጢአቶቻችንን ያስታውስብን ይሆን? ገላልጦስ ያወጣብን ይሆን? አንቶኒ ሆይኪማ የተባለ የሥነ-መለኮት ምኁር እንዲህ ሲል ያስቀምጠዋል፦ “የአማኞች … ውድቀቶችና ጉድለቶች … በፍርድ ቀን ላይ ይታያሉ። ነገር ግን – ይህ ደግሞ ወሳኝ ነጥብ ነው – የአማኞች ውድቀቶችና ጉድለቶች በፍርድ ቀን የሚገለጡት ይቅር የተባሉ፣ በደላቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ሙሉ በሙሉ የተሸፈኑ ኃጢአቶች ሆነው ነው።”
እንደዚህ ሳሉት፦ ራእይ 20፥12 “መጻሕፍት” እንደሚል፣ እግዚአብሔር ስለ እያንዳንዱ ሰው የተደራጀ ሰነድ አለው። ያደረጋችሁት ወይም የተናገራችሁት ነገር በሙሉ ከነውጤቱ ተቀድቶ ተቀምጧል (ማቴዎስ 12፥36)። “በክርስቶስ የፍርድ ወንበር” ፊት “በሥጋችን ለሠራነው በጎ ወይም ክፉ ሥራ” ፍርድን ለመቀበል ስንቆም፣ እግዚአብሔር ሰነዳችንን ይከፍትና የፈተና ወረቀቶቻችንን ሙሉ በሙሉ ከነውጤታቸው ይዘረግፋቸዋል (2ኛ ቆሮንቶስ 5፥10)። ከእያንዳንዱም ፈተና የተሳሳትናቸውን በሙሉ በአንድ ረድፍ፣ ልክ የመለስናቸውን ደግሞ በሌላ ረድፍ ይከምራቸዋል።
ከዚያም፣ ላዩ ላይ “የሕይወት መጽሐፍ” የሚል የተለጠፈበት ሌላ የታሸገ ፖስታ ይከፍትና ስማችሁን ይፈልጋል። በእምነት አማካኝነት በክርስቶስ ውስጥ ስለሆናችሁ፣ ስማችሁን ያገኘዋል። በስማችሁም ትይዩ፣ ከክርስቶስ መስቀል የተሰራ የእንጨት ክብሪት ይኖራል። ይህንንም ክብሪት ወስዶ ይለኩሰውና የወደቅናቸውና የተሳሳትናቸው ፈተናዎች የተከመሩበት ክምር ላይ ይወረውረዋል። ያቃጥለዋል። ከእንግዲህ አይኮንኑኗችሁም፣ ሽልማታችሁም እነርሱ ላይ የተመሠረተ አይሆንም።
ከዚያም “የሕይወት መጽሐፍ” ከሚለው ፖስታችሁ “ነፃ የሆነው የዘለዓለም ሕይወት ስጦታ” የሚል ማሕተም ያለበትን ፖስታ ያወጣና፣ የጥሩ ውጤት ክምሩ ላይ ያስቀምጠዋል (ማርቆስ 4፥24፤ ሉቃስ 6፥38)። ከዚያም ሁሉንም ሰነዶች አንስቶ እንዲህ ሲል ያውጃል፦ “በዚህ ሰነድ ምክንያት፣ ሕይወታችሁ ለአባቴ ጸጋ፣ ለደሜ ዋጋ እና ለመንፈሴ ፍሬ ምስክር ይሆናል። ሕይወታችሁ ዘላለማዊ መሆኑን ይመሰክራሉ። ሽልማታችሁንም የምታገኙት በእነዚህ መሠረት ነው። ወደ ጌታችሁ ዘላለማዊ ደስታ ግቡ።”