እንዴት በመንፈሱ መሞላት እችላለሁ? | መጋቢት 7

በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና። (ሮሜ 15፥4)

በመንፈስ ቅዱስ እንዴት ልንሞላ እንችላለን? በቤተ ክርስቲያናችን እና በራሳችን ላይ የማይቋረጥ ደስታ፣ ነፃነት እና ኅይል የሚሰጠንን፣ እንዲሁም በአጠገባችን ያሉትን ከልባችን እንድንወድ የሚያደርገንን የመንፈሱን ሙላት እንዴት ማየት እንችላለን?

መልሱ፦ አቻ የሌላቸውን እና ተስፋ ሰጪ የሆኑትን የእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት አሰላስሉ። ጳውሎስ ልቡን በተስፋ፣ በደስታ እና በፍቅር ሙሉ አድርጎ የቆየው በዚህ ነው (ሮሜ 15፥4)፤ “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።“

የተስፋው ማረጋገጫ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ከምናደርገው ማሰላሰል ይመነጫል። ይህ ደግሞ ከዘጠኝ ቁጥሮች ቀጥሎ ካለው እና መንፈስ ቅዱስ ተስፋ ይሰጠናል ከሚለው ዐረፍተ ነገር ጋር አይጋጭም (ሮሜ 15፥13)። ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ የቃሉ መለኮታዊ ጸሓፊ ነው። ቃሉ የሥራው ማስፈጸሚያ ነው። በተስፋ የሚሞላን፣ በራሱ ቃል ሲሞላን መሆኑ ምንም ግጭት አይፈጥርም ማለት ነው።

ተስፋ እንደ ሆድ ሕመም ድንገት ብቅ የሚል ውስብስብ ስሜት አይደለም። ተስፋ ማለት የመንፈሱ ቃል ወደ ፊት ሊፈጽመው ቃል የገባልን እጅግ ያማረ፣ ወደ ፊት እውነት እንደሚሆን ያለ እርግጠኝነት ነው። እናም በመንፈሱ ለመሞላት ብቸኛው መንገድ በቃሉ መሞላት ነው፤ የመንፈሱን ኅይል ለመያዝ ብቸኛው መንገድ በተስፋ ቃሉ ማመን ነው።

በተስፋ የሚሞላን ቃሉ ነውና፤ በደስታም የሚሞላን ተስፋው ነውና፤ ደስታችን ሞልቶ የሚትረፈረፈው ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን አድርገን ስንወድ ነውና። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ማለት ይህ ነው።