እግዚአብሔርን እንዴት ከፍ ከፍ ማድረግ ይቻላል? | ሕዳር 20

የእግዚአብሔርን ስም በዝማሬ አወድሳለሁ፤ በምስጋናም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። (መዝሙረ ዳዊት 69፥30)

ሁለት የማጉላት ዐይነቶች አሉ፤ የማይክሮስኮፕ ማጉላት እና የቴሌስኮፕ ማጉላት። ማይክሮስኮፕ ትንሽን ነገር ትልቅ ማስመሰል ይችላል። ቴሌስኮፕ ደግሞ በርቀት ያለን አንድ ግዙፍ ነገር፣ በእርግጥም እንደ ግዝፈቱ እንዲታይ ያደርገዋል።

ዳዊት “እግዚአብሔርን በምስጋና ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ” ሲል “ትንሹን አምላክ ትልቅ አስመስለዋለሁ” እያለ አይደለም። እያለ ያለው “ትልቁን አምላክ የእውነት ትልቅ የሆነውን ያህል ትልቅ ሆኖ እንዲታይ አደርጋለሁ” ማለቱ ነው።

ማይክሮስኮፕ እንድንሆን አልተጠራንም። ቴሌስኮፖች እንድንሆን ተጠርተናል። የገበያ ተቀናቃኛቸው ምርት ከእነርሱ እንደሚበልጥ ሲያውቁ፣ ምርታቸውን ከእውነታው አርቀው በጣም እንደሚያጋንኑ አጭበርባሪዎች እንድንሆን አልተጠራንም። ከእግዚአብሔር የሚልቅ ምንም እና ማንም የለም። እግዚአብሔርን የሚወዱ ሰዎች የተጠሩት ታላቅነቱን በሚመጥን መልኩ ገኖ እና ተደንቆ እንዲታይ ማድረግ ነው።

ለዚህም ነው በሕይወት ያለነው። ጴጥሮስ በ1ኛ ጴጥሮስ 2፥9 እንደሚናገረው፦ “እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእግዚአብሔርን ታላቅ ሥራ እንድታውጁ፣ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ እግዚአብሔር ለራሱ የለያችሁ ሕዝብ ናችሁ” ይለናል። የመዳናችንም ምክንያት ይህ ነው።

የክርስቲያን ኅላፊነት በዚህ ሊጠቃለል ይችላል፦ እግዚአብሔር እንደ ትልቅነቱ መጠን የሚያሳይ ሕይወት መኖር አለብን። ወሰን የሌለውን ብሩህ የእግዚአብሔር ክብር ባለጠግነት ለዓለም ለማሳየት ቴሌስኮፖች ሁኑ።

ለአንድ ክርስቲያን፣ እግዚአብሔርን ማጉላት ማለት ይህ ነው። ነገር ግን ያላያችሁትን ወይም በፍጥነት የምትረሱትን ነገር ማጉላት አትችሉም።

ስለዚህ፣ የመጀመሪያ ስራችን፣ የእግዚአብሔርን ታላቅነትና ቸርነት ማየትና ማስታወስ ነው። እናም “የልቤን ዐይኖች ክፈት!” ብለን ወደ እግዚአብሔር እንጸልያለን (ኤፌሶን 1፥18)፤ ለነፍሳችን ደግሞ “ነፍሴ ሆይ ውለታውንም ሁሉ አትርሺ” ብለን እንሰብካለን (መዝሙረ ዳዊት 103፥2)።