“ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥23)
ከክርስቶስ በላይ ኅጢአት የተደረገበትና የተበደለ ማንም የለም። የደረሰበት እያንዳንዱ በደልና ጥላቻ በፍጹም የማይገባው ነበር።
ክብር የሚገባው ሕይወት የክርስቶስን ያህል የኖረ የለም፤ ሆኖም ግን ከእርሱ በላይ የተዋረደ የለም።
ማንም ለማማረር፣ ለመበቀል እና ለመቆጣት መብት ቢኖረው፣ ከኢየሱስ የተሻለ ባለመብት የለም። ራሱን ግን እንዴት ገዛ? ህልውናቸውን በእጆቹ የያዘላቸው ወራዶች ፊቱ ላይ ሲተፉ እንዴት አስችሎት ዝም አለ? 1 ጴጥሮስ 2፥23 ለዚህ መልስ ይሰጠናል፦ “ሲሰድቡት መልሶ አልተሳደበም፤ መከራ ሲደርስበት አልዛተም፤ ነገር ግን በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን አሳልፎ ሰጠ።”
ከዚህ ጥቅስ የምንማረው አንድ ነገር፣ ኢየሱስ ራሱ ወደፊት ሊገለጥ ባለው የእግዚአብሔር ጻድቅ ፍርድ ጸጋ ላይ እምነት እንደነበረው ነው። ጉዳዩን ለእግዚአብሔር አሳልፎ ስለሰጠ፣ ለደረሰበት ኢሰብዓዊ ድርጊት ሁሉ ራሱ ሊበቀል አላስፈለገውም። በቀልን በእግዚአብሔር እጅ በመተው ለጠላቶቹ ፀለየ። “ኢየሱስም፣ “አባት ሆይ፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” አለ። እነርሱም ልብሱን በዕጣ ተከፋፈሉት” (ሉቃስ 23፥34)።
እኛ ራሳችን በዚህ መንገድ እንዴት መኖር እንደምንችል ለትምህርታችን እንዲሆን ጴጥሮስ ስለ ኢየሱስ እምነት ይህን በጭላንጭል ሊያሳየን እንዲህ ይላል፦ “የተጠራችሁትም ለዚሁ ነው፤ ምክንያቱም ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌን ሊተውላችሁ ነው” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥21)።
ቸሩ ዳኛ እግዚአብሔር የገባውን ቃል በማመን ኢየሱስ ምሬትንና በቀልን ካሸነፈ፣ እኛስ ከእርሱ እጅግ ያነሰ የማጉረምረም መብት ያለን ኀጢአተኞች፣ እንዴት የበለጠ ምሬታችንንና በቀላችንን ለእግዚአብሔር ልንተው ይገባናል?