“የሞት ማዕበል ከበበኝ፤ የጥፋትም ጐርፍ አሰጠመኝ። … የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው።” (2ኛ ሳሙኤል 22፥5፣ 31)
ኢዮብ በተፈጥሮ አደጋ 10 ልጆቹን ካጣ በኋላ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ሰጠ፥ እግዚአብሔርም ነሣ፤ የእግዚአብሔር ስም ቡሩክ ይሁን” (ኢዮብ 1፥21)። በመጽሐፉም መጨረሻ ላይ፣ በመንፈስ ቅዱስ የተመራው የመጽሐፉ ጸሐፊ በተፈጠረው ነገር ሁሉ ላይ ኢዮብ ያለውን መረዳት እንዲህ ሲል ያረጋግጥልናል፦ የኢዮብ ወንድሞችና እኅቶቹ “እግዚአብሔርም ካመጣበት መከራ ሁሉ አጽናኑት” (ኢዮብ 42፥11)።
ይህ ለእኛ በርካታ ወሳኝ አንድምታዎች ይኖሩታል። በየትኛውም ጊዜ፣ በዓለም እና በራሳችን ሕይወት ውስጥ ያሉትን መከራዎች – ልክ እንደ ሕንድ ውቅያኖሱ ዓይነት፣ በታሕሳስ 26፣ 2004 ዓ.ም የተከሰተው፣ 1.7 ሚሊዮን ሰዎችን ከቤታቸው ስላፈናቀለው፣ ግማሽ ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ስለተጎዱበት እና 230,000 ሰዎች ስለሞቱበት – በዓለም ታሪክ ከተመዘገቡ እጅግ አስከፊ ከሆኑ የተፈጥሮ አደጋዎች ውስጥ አንዱ ስለሆነው፣ ስለዚህ አደጋ ለምናስብ ለእኛ ብዙ ትምህርት ይኖረዋል።
ትምህርት አንድ፦ የመጨረሻው የበላይ እና አሸናፊ እግዚአብሔር እንጂ ሰይጣን አይደለም።
በኢዮብ መከራ ውስጥ የሰይጣን እጅ ነበረ፤ ነገር ግን ወሳኙ እጅ የእርሱ አልነበረም። ሰይጣን ኢዮብን እንዲያሰቃየው እግዚአብሔር ፈቅዶለታል (ኢዮብ 1፥12፤ 2፥6)። ነገር ግን ኢዮብና የኢዮብ መጽሐፍ ጸሐፊ፣ እግዚአብሔርን ወሳኝ መንስኤ አድርገው ይመለከቱታል። ሰይጣን ኢዮብን በቁስል ባሰቃየው ጊዜ፣ ኢዮብ ሚስቱን “መልካሙን ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀበልን፤ ክፉውንስ አንቀበልምን?” ብሏታል (ኢዮብ 2፥10)። የመጽሐፉ ጸሐፊም እነዚህን ሰይጣናዊ ቁስሎች “እግዚአብሔርም ያመጣበት መከራ” በማለት ጠርቷቸዋል (ኢዮብ 42፥11)። ስለዚህ ሰይጣን እውን ነው። ሰይጣን መከራን ያመጣል። ነገር ግን ሰይጣን የበላይ ወይም የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አይደለም። ሰይጣን በቁጥጥር ሥር ነው። እግዚአብሔር እንዲያደርግ ከፈቀደው በላይ ምንም ሊያደርግ አይችልም።
ትምህርት ሁለት፦ ሰይጣን በ2004 የገና በዓል ማግስት በህንድ ውቅያኖስ ላይ የተከሰተውን ያንን ከፍተኛ ሱናሚ አምጥቶ ቢሆን እንኳ፣ ከ200,000 በላይ ለሚሆነው የሰዎች ሞት ግን ውሳኔ አሳላፊው እግዚአብሔር እንጂ ሰይጣን አይደለም።
በኢዮብ 38፥8 እና 11 ላይ፣ እግዚአብሔር ኢዮብን፣ “ባሕር ከማሕፀን በወጣ ጊዜ፣ በር የዘጋበት ማን ነው?” ሲል መልስ የማያሻውን ጥያቄ በመጠየቅ፣ ከዚያም፣ “‘እስከዚህ ድረስ ትመጣለህ፤ ማለፍ ግን አትችልም፤ የዕቡይ ማዕበልህም ገደብ ይህ ነው’ አልሁት” በማለት በማዕበል ላይ ሥልጣን ያለው እርሱ እንደሆነ ይናገራል። መዝሙር 89፥8-9 ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ … የባሕርን ቍጣ ትቈጣጠራለህ፤ ሞገዱም ሲነሣ ጸጥ ታደርገዋለህ።” ኢየሱስም ያኔ በአስፈሪው ማዕበል ላይ የነበረው ሥልጣን፣ ዛሬም አለው። “እርሱም… ነፋሱንና የውሃውን መናወጥ ገሠጸ፤ በዚህ ጊዜ ነፋሱም ነውጡም ተወ፤ ጸጥታም ሆነ” ይለናል (ሉቃስ 8፥24)። በሌላ አነጋገር፣ ሰይጣን የመሬት መንቀጥቀጡን አምጥቶ ቢሆን እንኳ፣ እግዚአብሔር ማዕበሉን ማስቆም ይችል ነበር ማለት ነው። ነገር ግን አላስቆመውም።
ትምህርት ሦስት፦ በዚህ ዓለም ያሉ ደምሳሽ ጥፋቶች ፍርድንና ምሕረትን በአንድነት ያቅፋሉ።
የእግዚአብሔር ዓላማዎች ቀላል አይደሉም። ኢዮብ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚመላለስ ሰው ነበር፤ እናም መከራው የእግዚአብሔር ቅጣት አልነበረም (ኢዮብ 1፥1፣ 8)። የመከራው ንድፍ ማነጽ እንጂ ቅጣት አልነበረም (ኢዮብ 42፥6)። ያዕቆብ 5፥11 ላይ እንዲህ ይላል፦ “ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው።”
ሆኖም ግን የሞቱት የኢዮብ ልጆች ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ አናውቅም። ኢዮብ በርግጥ ስለ እነርሱ ግድ ይለው ነበር (ኢዮብ 1፥5)። እግዚአብሔር በፍርዱ ሕይወታቸውን ወስዶ ሊሆን ይችላል። አናውቅም።
ይህ እውነት ከሆነ ታዲያ፣ ይኸው ተመሳሳይ ጥፋት፣ በመጨረሻ ለኢዮብ ምሕረት፣ በልጆቹ ላይ ደግሞ ፍርድ ሆኖ ተገኝቷል። ይህ ድርብ ዓላማ ለሁሉም ጥፋቶች ይሠራል። ፍርድንና ምሕረትን፣ ቅጣትና ማነጽን በአንድነት በውስጡ ይይዛል። መከራ ሲብስም ደግሞ ሞት፣ ሁለቱም በአንድ ጊዜ ፍርድም ምሕረትም ሊሆኑ ይችላሉ።
ለዚህ በጣም ግልጽ የሆነው ምሳሌ የኢየሱስ ሞት ነው። የኢየሱስ ሞት ፍርድም ምሕረትም ነበር። የራሱን ሳይሆን የእኛን ኃጢአት ስለ ተሸከመ በኢየሱስ ላይ ፍርድ ነበር። ቅጣታችንን እንደተቀበለ እና ጽድቃችን እንደሆነ ለምናምን ለእኛ ደግሞ ምህረት ነበር (ገላትያ 3፥13፤ 1ኛ ጴጥሮስ 2፥24፤ 2ኛ ቆሮንቶስ 5፥21)።
ሌላው ምሳሌ፣ በአዳምና በሔዋን ውድቀት ምክንያት በዚህ ምድር ላይ የመጣው እርግማንና መከራ ነው። በክርስቶስ የማያምኑት እንደ ፍርድ ይቀበሉታል፣ ለአማኞች ግን ምንም እንኳ ህመም የተሞላበት ቢሆን፣ የምህረት እንዲሁም ለክብር የሚደረግ ዝግጅት ይሆንላቸዋል። “ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተዳርጓል፤ ይኸውም በራሱ ምርጫ ሳይሆን፣ ለተስፋ እንዲገዛ ካደረገው ከፈቃዱ የተነሣ ነው” ይለናል (ሮሜ 8፥20)። በዚህ የምናየው የእግዚአብሔርን አገዛዝ ነው። ለዚህ ነው በምድር ላይ ማዕበሎች እና ሱናሚዎች ያሉት። ነገር ግን ይህ “ለከንቱነት መገዛት” ለተስፋ ነው።
ትምህርት አራት፦ ክርስቶስ ለልጆቹ የሚሰጠው ልብ፣ በየትኛውም እምነት ላሉ፣ በመከራ ውስጥ ለሚያልፉ ለሁሉም ሰዎች የሚራራ ልብ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ “ከሚያዝኑም ጋር ዕዘኑ” ሲል፣ “እግዚአብሔር ካስለቀሳቸው በቀር” የሚል አይጨምርም (ሮሜ 12፥15)። የኢዮብ አስተዛዛኞች ብዙ ከመናገር ይልቅ ከኢዮብ ጋር ቢያለቅሱ የተሻለ ባደረጉ ነበር። ታዲያ በመጨረሻ የኢዮብ ሥቃይ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ስናውቅ ይህ አይለወጥም? በፍጹም፣ ከሚሰቃዩ ጋር ማልቀስ ተገቢ ነው። ማንም ያምጣው ማን ህመም፣ ህመም ነው። ሁላችንም ኃጢአተኞች ነን። ሐዘኔታ የሚመነጨው ከመከራው መንስኤ ሳይሆን የመከራው ተካፋይ ከመሆን ነው። በዚህ ደግሞ ሁላችንም አንድ ላይ ነን።
ትምህርት አምስት፦ በመጨረሻም፣ የማይገባቸው ቢሆን እንኳ በመከራ ለሚያልፉ ምህረትን እንድናሳይ ክርስቶስ ይጠራናል።
ምሕረት ማለት “ያልተገባ እርዳታ” ማለት ነው። ሉቃስ 6፥27 “ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚጠሏችሁም መልካም አድርጉ” ይለናል። ጠላቶቹ እያለን ክርስቶስ ስለ እኛ በመሞት ያደረገልን ይህንኑ ነው (ሮሜ 5፥10)። ይህን ምሳሌ በመከተል እና ራሱ ክርስቶስ የሚሰጠን አቅም ላይ በመመርኮዝ፣ እኛም እንዲሁ እናደርጋለን።