እግዚአብሔር ምን ያህል ሊባርከን ይፈልጋል? | ሰኔ 16

እግዚአብሔር አንተንም በማበልጸግ ደስ ይለዋልና። (ዘዳግም 30፥9)

እግዚአብሔር እየተቆጨ አይባርከንም። የእግዚአብሔር ቸርነት የሆነ ዓይነት ጉጉት በውስጡ አለው። እኛ ወደ እርሱ እስክንመጣ ድረስ አይጠብቅም። ራሱ ይፈልገናል፤ ምክንያቱም ለእኛ መልካምን ማድረግ ደስታው ነው። እግዚአብሔር እኛን ቁጭ ብሎ እየጠበቀን አይደለም፤ ይልቁንም እየተከታተለን ነው። እንደውም የመዝሙር 23፥​6 ቀጥተኛ ትርጉም ይህ ነው፦ “በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ በጎነትና ምሕረት በርግጥ ይከተሉኛል።”         

እግዚአብሔር ምሕረት ማድረግን ይወድዳል። ልድገመው። እግዚአብሔር ምሕረት ማድረግን ይወድዳል። ለሕዝቡ መልካም ለማድረግ ባለው ፍላጎቱ የሚያመነታ፣ ቆራጥ ያልሆነ ወይም መወሰን ያቃተው አምላክ አይደለም። ቁጣው በጠንካራ የብረት ቁልፍ እንደተቆለፈ በር ለመፍሰስ ጊዜ ይፈጃል፣ ምህረቱ ግን የተያዘው እንደ ጸጉር በቀጠነ ስስ ክር ነው። ለምሕረት የቸኮለ ነው። ይህንን ነው እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ወርዶ፦ “እግዚአብሔር ርኅሩኅ ቸር አምላክ፣ እግዚአብሔር ለቍጣ የዘገየ፣ ፍቅሩና ታማኝነቱ የበዛ” በማለት ለሙሴ ስለማንነቱ ሲነግረው ይህንን ማለቱ ነበር (ዘጸአት 34፥6)። በኤርምያስ 9፥24 ላይም፣ “በምድር ላይ ምሕረትን፣ ፍትሕንና ጽድቅን የማደርግ መሆኔን በመረዳቱ፣ በዚህ ይመካ፤ እኔ በእነዚህ ነገሮች፣ እደሰታለሁና” ብሎ ሲናገር ይህንን ማለቱ ነበር።

እግዚአብሔር ለቁጣ የፈጠነ ብስጩ አምላክ አይደለም። ቁጣው በቀላሉ አይነድድም። ይልቁንም የሚያስደስተውን ለማግኘት ወሰን የሌለው፣ የማያቋርጥ ትጋትና ጉጉት አለው።

ይህንን መረዳት ለእኛ ከባድ ነው፤ ምክንያቱም እኛ ወደዚህ ልናድግ ቀርቶ የየዕለት ውጣ ውረድን ለመቋቋም ብቻ እንኳ በየቀኑ መተኛት አለብን። ስሜታችን ይዋዥቃል። አንድ ቀን እንሰለቻለን፣ ተስፋም እንቆርጣለን። ሌላ ቀን ደግሞ ተስፋ የተሞላን እና ደስተኞች እንሆናለን።

እኛ ልክ በዘፈቀደ ብቅ ብለው እንደሚንቦቀቦቁ እና እንደሚፈናጠቁ ትንንሽ ፍል ውሃዎች ነን። እግዚአብሔር ግን ከዓመት እስከ ዓመት ያለማቋረጥ እንደሚፈሰው እንደ ታላቁ የናያጋራ ፏፏቴ ነው። በካናዳ የሚገኘው ይህ ፏፏቴ በየደቂቃው 186 ሚሊዮን ኪሎ የሚመዝን ውሃን ከገደል ጋር እያጋጨ ሲወረውር ይውላል፣ ያድራል። ቆማችሁ ስትመለከቱት ትውሉና፣ መቼም ከዛሬ ነገ ያልቃል፣ ከዓመት ዓመት በዚህ ኃይሉ መቀጠል አይችልም ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ግን መቼም አይቆምም።

እግዚአብሔርም ለእኛ መልካምን የሚያደርገው እንዲሁ ነው። አይታክትም። ፈጽሞም አይሰለችም። እንደ ታላቁ አባይ ፏፏቴና እንደ ግዙፉ ናያግራ፣ ጸጋው መጨረሻ የለውም።