በትዕግሥት የጸኑትን የተባረኩ አድርገን እንደምንቈጥር ታውቃላችሁ፤ ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው። (ያዕቆብ 5፥11)
ከእያንዳንዱ ህመም እና ጉዳት በስተጀርባ ከሁሉ የበላይ የሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ አለ። ሰይጣን የለበትም ለማለት አይደለም፤ እርሱ ሁልጊዜ አጥፊ አጀንዳን አንግቦ በአንድም ወይም በሌላ መንገድ መሳተፉ አይቀርም (ሐዋሪያት ሥራ 10፥38)። የእርሱ ኃይል ግን ዕጣ ፈንታን የመወሰን አቅም የለውም። ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ አንዳች ሊሰራ አይችልም።
ኢዮብም የታመመበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ክፍሉ በኢዮብ ላይ በሽታ በመጣ ጊዜ፣ “ሰይጣን … ኢዮብንም ከእግር ጥፍሩ እስከ ራስ ጠጒሩ በክፉ ቍስል መታው” በማለት ግልጽ ያደርገዋል (ኢዮብ 2፥7)። ሚስቱ እግዚአብሔርን እንዲረግም ለመነችው። ኢዮብ ግን “መልካሙን ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀበልን፣ ክፉውንስ አንቀበልምን?” አለ (ኢዮብ 2፥10)። እንደገናም፣ በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ይህን የጻፈው የመጽሐፉ ጸሐፊ፣ “በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም” በማለት ኢዮብን አመስግኖታል (ኢዮብ 1፥22)።
ይህ ማለት እግዚአብሔር በሰይጣን ላይ በሉዓላዊነት ይገዛል ማለት ነው። ሰይጣን ምናባዊ ነገር አይደለም፤ በመከራዎቻችንም ውስጥ እጁ ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ፍጻሜያችንን እና ዕጣ ፈንጣችንን የሚወስን እጅ አይደለም። በኢዮብ መከራ ሁሉ እግዚአብሔር መልካም ዓላማ እንደነበረው ያዕቆብ በግልጽ ተናግሯል፦ “ኢዮብ እንዴት ታግሦ እንደ ጸና ሰምታችኋል፤ ጌታም በመጨረሻ ያደረገለትን አይታችኋል። ጌታ እጅግ ርኅሩኅና መሓሪ ነው” (ያዕቆብ 5፥11)።
ስለዚህ ሰይጣን እጁ ቢኖርበትም ገዢው ዓላማ ግን የእግዚአብሔር ነበር፤ ዓላማውም “ርኅራኄ እና ምሕረት” የሞላው ነበር።
ከ 2ኛ ቆሮንቶስ 12፥7 የምንማረው ትምህርት ይኸው ነው፤ ጳውሎስ የሥጋው መውጊያ “የሰይጣን መልእክተኛ” እንደነበር ፣ ሆኖም ግን የመውጊያው ግቡ እንዲቀደስ እና እንዳይታበይ መሆኑንን እንማራለን። “ከዚህ ታላቅ መገለጥ የተነሣ እንዳልታበይ የሥጋዬ መውጊያ፣ እርሱም የሚያሠቃየኝ የሰይጣን መልእክተኛ ተሰጠኝ” ይላል።
መቼም በመከራ ውስጥ ትህትናን ማስተማር የሰይጣን ግብ አይደለም። ስለዚህ ይህ ግብ የእግዚአብሔር ነው። ይህም ማለት፣ እግዚአብሔር በጳውሎስ ሕይወት ውስጥ ያለውን መልካም ዓላማውን ለመፈጸም ሰይጣንን እየተጠቀመበት ነው ማለት ነው። ሰይጣን በእግዚአብሔር የተመሩጥትን ልጆቹን ሊያጠፋ ከቶ አይቻለውም። እንዲያውም እግዚአብሔር አምላክ ከሰይጣን የሚሰነዘሩትን ጥቃቶች ሁሉ በመጨረሻ በራሱ ላይ ይመልስበታል፤ ለእኛ ጥቅምም ያደርገዋል።