ይቅርታን እንዴት መጠየቅ እንችላለን? | ግንቦት 4

“ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኀጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው።” (1ኛ ዮሐንስ 1፥9)

በስነ-መለኮት ትምህርት ቤት እያለው ከአስተማሪዎቼ አንዱ፣ “የአንድን ሰው ግላዊ ስነመለኮት ለመፈተን አዋጭ የሆነው መንገድ፣ በፀሎት ሕይወቱ ላይ ያለውን ተፅዕኖ መመልከት ነው” ብሎ ሲናገር መስማቴን አስታውሳለሁ።

ይህ እውነት ነው እንድል ያስገደደኝ ደግሞ በራሴ ህይወት ውስጥ ሲሆን ያየሁት ነገር ነው። ባለቤቴ ኖኤል እና እኔ ገና መጋባታችን ነበር። እናም በየዕለቱ ምሽት ላይ በጋራ መፀለይን እየተለማመድን ነበር። ታዲያማ እየተማርኳቸው የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ኮርሶች፣ የግል ስነ መለኮቴ ላይ ለውጥ በሚያመጡበት ጊዜ፣ ፀሎቶቼም እንደዚያው እየተቀየሩ መሆናቸውን አስተዋልኩ።

ምናልባትም በዚያ ወቅት ያስተዋልኩት ትልቅ ለውጥ፣ በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ስቀርብ፣ ልመናዬን ሁሉ በእርሱ ክብር መሰረት ላይ ማድረግን መማሬን ነበር። ፀሎቴን ስጀምር “ስምህ ይቀደስ” በማለት መጀመርን፣ ስጨርስ ደግሞ “በኢየሱስ ስም” ብሎ መጨረስን እየተማርኩ ነበር። ይህንንም ሳደርግ፣ የእግዚአብሔር ስም መክበር የፀሎቴ ዓላማ እና መሰረት ነው እያልኩ ነበር።

ከዚያ ደግሞ፣ ንሰሃ መግባት ሊመሠረት የሚገባው የእግዚአብሔርን ምህረት በመለመን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ የልጁ ታዛዥነት ለኛ እንዲቆጥርልን ከእርሱ ፍትህን መለመን ጭምር መሆኑ ሲገባኝ ደግሞ በህይወቴ ታላቅ ጥንካሬ ተፈጠረ። እግዚአብሔር ታማኝና ጻድቅ ስለሆነ ኃጢአታችንን ይቅር ይለናል (1ኛ ዮሐንስ 1:9)።

ከብሉይ ኪዳን ይልቅ፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የኀጢአታችን ስርየት መሰረት ይበልጥ ተብራርቷል። ይሁን እንጂ ይህ መሰረት፣ ማለትም እግዚአብሔር ለስሙ ያለው መሰጠት፣ ፈጽሞ አልተቀየረም።

ጳውሎስ፣ የክርስቶስ ሞት፣ ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው ብሎ ያስተምራል (ሮሜ 3:25-26)።

በሌላ አነጋገር፣ ክርስቶስ የሞተው እግዚአብሔር ኢ-ፍትሐዊ አለመሆኑን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማወጅ ነው። በደለኛ ኀጢአተኞችን እንዲያው እንደቀላል ለኢየሱስ ሲል ለቀቃቸው እያለን አይደለም። ይልቁንም፣ ኢየሱስ የሞተው ሞት “ለኢየሱስ ሲባል” ይቅር ማለትን እና “ለእግዚአብሔር ስም ሲባል” ይቅር ማለትን አንድ የሚያደርግ ሞት ነው። አያችሁ፣ ፍትሕ አልተጓደለም። የእግዚአብሔር ስም፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ፣ እና የእግዚአብሔር ፍትሕ በዚህ እግዚአብሔርን በሚያከብር የክርስቶስ መስዋዕትነት ውስጥ በግልጽ ታይቷል።

ኢየሱስ ለሞት በተቃረበባት በመጨረሻዋ ሰዓት ላይ እንዳለው ማለት ነው፤ “አሁንስ ነፍሴ ተጨነቀች፤ ምን ልበል? አባት ሆይ፤ ከዚህች ሰዓት ብታድነኝስ? ይሁን፤ የመጣሁት ለዚህች ሰዓት ነውና። አባት ሆይ፤ ስምህን አክብረው” (ዮሐንስ 12:27-28)። ያደረገውም ያንኑ ነው። ያደረገበትም ምክንያት፣ እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው (ሮሜ 3:26)።