የኃጢአትን መሻት መቃወሚያ መንገድ | ሐምሌ 22

ሙሴ ካደገ በኋላ፣ የፈርዖን የልጅ ልጅ መባልን በእምነት እምቢ አለ። ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ፣ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራን መቀበል መረጠ። ከግብፅ ሀብት ይልቅ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እጅግ የሚበልጥ ሀብት መሆኑን ተገነዘበ፤ ወደ ፊት የሚቀበለውን ብድራት ከሩቅ ተመልክቶአልና ” (ዕብራውያን 11፥24-26)።

ይህንን ጥቅስ አጠር አድርገን ብናስቀምጠው፣ “ሙሴ በእምነት… ለጥቂት ጊዜ በኀጢአት የሚገኝ ደስታ [ተወ] … ብድራቱን ከሩቅ ተመልክቶአልና” ብለን ልናሳጥረው እንችላለን (ዕብራውያን 11፥24-26)።

እምነት “በጊዜያዊ ተድላ” አይረካም። ዛሬ ታይቶ ነገ በሚጠፋ የውሸት ሞቅታ አይታለልም። ለዘላለም ዘላቂ የሆነን ደስታ ያለማቋረጥ ይፈልጋል። የእግዚአብሔርም ቃል፣ “በአንተ ዘንድ የደስታ ሙላት፣ በቀኝህም የዘላለም ፍስሓ አለ” ይላል (መዝሙር 16፥11)። ስለዚህም እምነት አታላይ በሆነ የኃጢአት ደስታ ተጠልፎ አይወድቅም። ከመንገዱም ስቶ አይወጣም። የላቀውን የደስታ ጥግ ለማግኘት በሚያደርገውም ጥረት በቀላሉ ተስፋ አይቆርጥም።

እምነት ለእግዚአብሔር ያለውን ረሃብ መጽሐፍ ቅዱስ ይመግባል። ይህንንም ሲያደርግ ልባችንን ከአታላዩ የፍትወት ጣዕም ይለየዋል።

መጀመሪያ ላይ በልቤ ያለው የፍትወት ምኞት የንጽሕናን መንገድ ከተከተልኩ ታላላቅ እርካታዎችን የማጣ እንዲመስለኝ በማድረግ ማታለል ይሞክራል። ነገር ግን ያ ሲሆን፣ የመንፈስን ሰይፍ አንሥቼ መዋጋት እጀምራለሁ።

  • ከፍትወት ምኞት ይልቅ ዓይኖቼን አውጥቼ መጣል እንደሚሻለኝ ቃሉ ይነግረኛል (ማቴዎስ 5፥29)።
  • ንጹሕና ተወዳጅ የሆነውን ከሁሉ የላቀውንም ነገር ካሰብኩ፣ የእግዚአብሔር ሰላም ከእኔ ጋር እንደሚሆን ቃል ይገባልኛል (ፊልጵስዩስ 4፥8-9)።
  • ስለ ሥጋ ማሰብ ሞትን የሚያመጣ መሆኑንና ስለ መንፈስ ግን ማሰብ ሕይወትንና ሰላምን እንደሚያመጣ ያሳውቀኛል (ሮሜ 8፥6)።
  • ሥጋዊ ምኞት ነፍሴን እንደሚዋጋ (1ኛ ጴጥሮስ 2፥11)፣ ደግሞም የዚህ ዓለም ደስታ የመንፈስን ሕይወት እንደሚያጠፋ ያስጠነቅቀኛል (ሉቃስ 8፥14)።
  • ከሁሉ በላይ ግን፣ እግዚአብሔር በቅንነት ለሚሄዱት መልካም ነገርን እንደማይከለክልና ልበ ንጹሐን እግዚአብሔርን እንደሚያዩት ያበስረኛል (መዝሙር 84፥11ማቴዎስ 5፥8)።

እምነታችን በእግዚአብሔር ሕይወት እና ሰላም እንዲረካ ተግተን ስንጸልይ፣ የመንፈሱ ሰይፍ በፍትወት መርዝ ላይ የተለጠፈውን የውሸት ብልጭልጭ ፈቅፍቆ ይጥለዋል። ገዳይነቱንም ያጋልጠዋል። በእግዚአብሔርም ጸጋ የአማላይነት ኃይሉ ለዘለዓለም ይሰባበራል።