ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው። (መዝሙር 119፥103)
ክርስትናን መቼም ቢሆን ወደ ፍላጎት ሟሟያነት እንዳታወርዱት። ክርስትና የትዕዛዛት ክምር፣ ወይም ወደፊት መሆን የምንፈልጋቸው ነገሮች ዝርዝር አይደለም። ክርስትና የፍቅራችን እና የደስታችን ማዕከል የሆነውን ሁሉ የሚገለባብጥ እውነት ነው። የምንወደውን፣ ደስ የሚያሰኘንን እና የሚጣፍጠንን ነገር ሁሉ የሚገራ ታላቅ ምስጢር ነው።
ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመጣ፣ ሰዎች በሚወድዷቸው ነገሮች ለሁለት ተከፍለው ነበር። “ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጣ፤ ሰዎች ግን ሥራቸው ክፉ ስለ ነበረ፣ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ወደዱ” ይለናል (ዮሐንስ 3፥19)። ጻድቃን እና ኅጢተኞች የሚለዩት በደስታ ምንጫቸው ሆኖ እናገኛለን። አንደኛው ቡድን የእግዚአብሔርን በኢየሱስ አማካኝነት መገለጥ ሲወድድ፣ ሌላኛው ደግሞ የዓለም መንገድ ወደደ።
ስለዚህ አንድ ሰው “በእግዚአብሔር ቃል እንዴት ደስ ልሰኝ?” ብሎ ቢጠይቀኝ፣ ሁለት ተያያዥ መልሶች ይኖሩኛል፦
- የልባችሁ ምላስ አዲስ መቅመሻዎች እንዲኖሩት ጸልዩ የሚል ሲሆን፣
- እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስለገባቸው አስደናቂ የተስፋ ቃሎች አሰላስሉ የሚል ነው።
“ቃልህ ለምላሴ ምንኛ ጣፋጭ ነው! ለአፌም ከማር ወለላ ይልቅ ጣዕም አለው” ያለው መዝሙረኛ፣ ቀደም ብሎ፣ “ከሕግህ ድንቅ ነገርን እንዳይ፣ ዐይኖቼን ክፈት” ብሏል (መዝሙር 119፥103፣ 119፥18)። ይህን ያለው፣ ክብሩን የምናይበት መንፈሳዊ ዐይንም ሆነ ቅድስናውን የምንቀምስበት የልብ ምላስ፣ የእግዚአብሔር ስጦታ ስለሆነ ነው። ማንም በተፈጥሮው ለእግዚአብሔር ጥበብ አይራብም፣ ደስም አይሰኝበትም።
ነገር ግን ስትጸልዩ፣ እግዚአብሔር በቃሉ ሊያደርግላችሁ ቃል የገባቸውን ነገሮች እያሰላሰላችሁ ጸልዩ። የኀያሉ አምላክ እርዳታ ዛሬና ለዘላለም እንደማይለያችሁ በማሰብ ዘወትር በፊቱ ቅረቡ። መዝሙር 1፥3-4 ቃሉን የሚያሰላስል ሰው፦ “… በወራጅ ውሃ ዳር እንደ ተተከለች፣ ፍሬዋን በየወቅቱ እንደምትሰጥ፣ ቅጠሏም እንደማይጠወልግ ዛፍ ነው፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” ይለናል። “ክፉዎች ግን እንዲህ አይደሉም፤ ነገር ግን ነፋስ ጠራርጎ እንደሚወስደው፣ ገለባ ናቸው።”
ከማይረባ ገለባ ወደማይጠወልግ ዛፍ የሚቀይር መጽሐፍ ማንበብ የማያስደስተው ማነው? ማንም ሰው ስር የሌለው፣ ክብደት የሌለው፣ ጥቅም የሌለው ባዶ ገለባ መሆን አይፈልግም። ሁላችንም ጠቃሚና ፍሬያማ ሰዎች ለመሆን ጥልቅ ጥበብ ከሚገኝበት የእውነት ወንዝ ብንቀዳ እንወዳለን።
ያ የእውነት ወንዝ የእግዚአብሔር ቃል ነው። በእርግጥም ታላላቅ የሚባሉ ቅዱሳን ሁሉ በዚህ ቃል ታላቅ ሆነዋል።