እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። (1ኛ ጴጥሮስ 5፥7)
መዝሙር 56፥3 “ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ እምነቴን በአንተ ላይ አደርጋለሁ” ይላል።
“ፍርሀት በፍጹም አይዘኝም” እንደማይል እናስተውል። ፍርሃት ይመጣል፤ ውጊያውም ይጀመራል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ አማኞች ምንም ጭንቀት አያገኛቸውም አይልም። ይልቅ ጭንቀት ሲመጣ እንዴት እንደምንዋጋ ይነግረናል።
ለምሳሌ 1ኛ ጴጥሮስ 5፥7 እንዲህ ይላል፦ “እርሱ ስለ እናንተ ስለሚያስብ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት።” በጭራሽ ምንም ጭንቀት አይሰማችሁም አይልም። ጭንቀታችሁን ሁሉ ግን በእግዚአብሔር ላይ ጣሉት ይላል። መኪና እየነዳችሁ ጭቃው መስታወታችሁን ሲሸፍን እና ለጊዜው መንገዱ አልታይ ብሏችሁ በጭንቀት ግራ ስትጋቡ፣ ውሃ ረጭታችሁ የመስታወት መጥረጊያውን አንቀሳቅሱ።
ስለዚህ ሁልጊዜ ለሚጨነቅ ሰው የምሰጠው ምላሽ ይህ ነው፦ ይብዛ ይነስም የተለመደ ስሜት ነው። ቢያንስ ለእኔ ከጉርምስና ዕድሜዬ ጀምሮ ያለ ነው። ዋናው ነገር ይህ ነው፦ ታዲያ ጭንቀትን እንዴት እንዋጋ?
ለዚህ ጥያቄ መልሱ፦ ጭንቀትን የምንዋጋው ካለማመን ጋር በመታገል እና እምነትን ወደፊት በሚገለጠው ጸጋ ላይ ለማሳረፍ በመታገል ነው። ሆኖም ይህን “መልካሙን ገድል” (1ኛ ጢሞ. 6፥12፣ 2ኛ ጢሞ. 4፥7) የምትጋደልበት መንገድ፣ እግዚአብሔር ወደፊት ስለሚገለጠው ጸጋ የሚሰጠውን ማረጋገጫ በማሰላሰል እና የመንፈሱን እርዳታ በመጠየቅ ነው።
የመስታወት መጥረጊያዎቹ የአለማመንን ጭቃ የሚያጸዱ የእግዚአብሔር ተስፋዎች ናቸው፤ የመስታወት ማጠቢያ ውሃው የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ነው። የጭንቀት ኃጢአትን ጨምሮ ከኃጢአት ለመላቀቅ የሚደረገው ጦርነት የሚካሄደው “በመንፈስ በመቀደስና በእውነትም በማመን” ነው (2ኛ ተሰሎንቄ 2፥13)።
የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እና የእውነት ቃል፦ እነዚህ እምነትን የሚገነቡ ታላላቅ መሣሪያዎች ናቸው። ያለ መንፈስ ቅዱስ የማለስለስ ሥራ፣ የቃሉ መጥረጊያዎች በመስታወቱ ላይ ያለውን ያለማመን ቆሻሻ ሳያፀዱ ይቦጫጭራሉ።
ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው፤ መንፈስና ቃል። የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች እናነባለን፤ ለመንፈሱ እርዳታም እንጸልያለን። እግዚአብሔር ለእኛ ያቀደውን ደኅንነት ለማየት እንድንችል መስታወቱ በመንፈሱ አማካኝነት ሲጸዳ፣ እምነታችንም እየጠነከረ ይሄዳል፤ የጭንቀት መንገዳገድም ይቀራል (ኤርምያስ 29፥11)።