ሕይወታችንን እንዴት እንጥላ? | ግንቦት 21

እውነት እላችኋለሁ፤ የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች ብቻዋን ትቀራለች፤ ብትሞት ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች። ሕይወቱን የሚወድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል። (ዮሐንስ 12፥24-25)

“ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል” ማለት ምን ማለት ነው?

ይህ ማለት፣ ቢያንስ፣ በዚህ ዓለም ስላለው ሕይወታችሁ አብዝታችሁ አታስቡም ወይም አትጨነቁም ማለት ነው። በዚህኛው ሕይወታችሁ ምንም ቢፈጠር፣ ያን ያህል ግድ አይላችሁም፣ ሁሉ ነገራችሁ እዚህ ምድር ላይ በሚፈጠረው ነገር አይንጠለጠልም።

  • ሰዎች ስለ እናንተ ጥሩ ቢያወሩ፣ ምንም አይደለም።
  • ቢጠሏችሁ፣ ምንም አይደለም።
  • ብዙ ሀብት ቢኖራችሁ፣ ምንም አይደለም።
  • ምንም ባይኖራችሁም፣ ምንም አይደለም።
  • ብትሰደዱ ወይም ውሸት ቢወራባችሁ፣ ምንም አይደለም።
  • ታዋቂ ብትሆኑ ወይም ማንም ባያውቃችሁ፣ ምንም አይደለም።
  • በእርግጥ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ምንም አይደሉም።

የኢየሱስ ንግግር ግን በዚህ አያበቃም፣ ከረር ያለ ነው። እያዘዘን ያለው ያለ ፍላጎታችን ወደ እኛ የመጡ ሁኔታዎችን እንድንታገስ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱን መርጠን እንድንከተለው ጭምር ነው። “የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ” ይላል (ዮሐንስ 12፥26)። ወዴት? እርሱ እየሄደ የነበረው ወደ ጌቴሴማኒና ወደ መስቀሉ ነበር።

ኢየሱስ፣ “ከእኔ ጋር ስለሞታችሁ፣ ነገሮች ቢከብዱባችሁ እንኳ አታካብዱ” እያለን አይደለም። እርሱ እያለን ያለው፣ “ከእኔ ጋር ለመሞት ምረጡ። እኔ መስቀሉን እንደመረጥኩ እናንተም በዚህ ዓለም ያላችሁን ሕይወት ለመጥላት ምረጡ“ ነው።

“ሊከተለኝ የሚወድ ራሱን ይካድ፣ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ሲል ይሄን እያለ ነው (ማቴዎስ 16፥24)። መስቀሉን እንድንመርጥ ይጠራናል። መስቀል ላይ የሚደረገው አንድ ነገር ብቻ ነው። ሰው ይሞትበታል። “መስቀሉን መሸከም” ማለት የስንዴ ቅንጣት መሬት ላይ ወድቃ እንደምትሞት፣ እንደዚያው መሞት ማለት ነው። እናም፣ ጥሪው ይህ ነው፦ መስቀሉን ምረጡ።

ግን ለምን? መልሱ፦ ለወንጌሉ አገልግሎት የተለየ ቆራጥነት እንዲኖረን ነው። ጳውሎስም እንዲህ ብሏል፦ “ከጌታ ከኢየሱስ የተቀበልሁትን ሩጫዬንና የእግዚአብሔርን የጸጋ ወንጌል የመመስከር አገልግሎቴን ብፈጽም፣ ለእኔ ሕይወቴ ከምንም እንደማይቈጠር እንደ ከንቱ ነገር ናት” (ሐዋርያት ሥራ 20፥24)። ጳውሎስ እንዲህ እያለ ይመስላል፦ “ለከበረው የእግዚአብሔር ጸጋ እስከኖርኩ ድረስ፣ እኔ ምንም ብሆን ምንም አይደለም።” እኛም እንዲህ የምንልበት ጸጋ ይብዛልን።