ለማያምኑት እንዴት መማጸን ይቻላል? | ሰኔ 20

ወንድሞች ሆይ፤ ስለ እስራኤላውያን የልቤ ምኞት፣ እግዚአብሔርንም የምለምነው እንዲድኑ ነው። (ሮሜ 10፥1)

እግዚአብሔር የእስራኤልን ልብ እንዲለውጥ እና መዳን እንዲሆንላቸው ጳውሎስ ይጸልያል። ይድኑ ዘንድ ይጸልይላቸዋል! ለውጥ የሚያመጣ ጣልቃ ገብነት እግዚአብሔር እንዲገባ ይለምናል። እኛም ላልዳኑ ሰዎች መጸለይ ያለብን በዚህ መንገድ ነው።

የእግዚአብሔርን የአዲሱን ኪዳን ተስፋዎች ይዘን፣ በልጆቻችን፣ በጎረቤቶቻችን፣ እንዲሁም ዓለም ላይ ባሉ የወንጌል ተልዕኮ ሜዳዎች ሁሉ ላይ እግዚአብሔር እንዲፈጽመው መለመን አለብን።

  • እግዚአብሔር ሆይ፣ የድንጋይን ልብ ከውስጣቸው አውጣና አዲስን የሥጋ ልብ ስጣቸው። (ሕዝቅኤል 11፥19)
  • ይወዱህ ዘንድ ልባቸውን ግረዝ! (ዘዳግም 30፥6)
  • አባት ሆይ፣ መንፈስህን በእነርሱ ውስጥ አኑርና በሥርዓትህ እንዲሄዱ አድርጋቸው። (ሕዝቅኤል 36፥27)
  • ከዲያብሎስ ወጥመድ ያመልጡ ዘንድ፣ ንስሓን ስጣቸው፤ ደግሞም እውነትን ወደ ማወቅ ምራቸው። (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥​25–26)
  • ወንጌልን እንዲያምኑ ልባቸውን ክፈት! (ሐዋርያት ሥራ 16፥14)

ልባቸው የደነደነ ኃጢአተኞችን ለመምረጥ እና ወደ ድነት ለማምጣት እግዚአብሔር ሉዓላዊ ስልጣን እና ኃይል እንዳለው ስናምን፣ ያን ጊዜ ታላላቅ በሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋዎች በመተማመን ያለማቋረጥ ለጠፉ ሰዎች መዳን መጸለይ እንችላለን።  

እንደዚህ ዓይነት ጸሎት እግዚአብሔር ብቻውን አዳኝ እንደሆነ፣ መራጭ እንደሆነ፣ ሉዓላዊ እንደሆነ በማወጅ የአምላክነቱን መብትና ክብር ይሰጠዋል። በዚህም እግዚአብሔር ደስ ይሰኛል።