ለእግዚአብሔር ምን ልክፈለው? | መስከረም 2

ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር ምን ልክፈለው? የመዳንን ጽዋ አነሣለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ። በሕዝቡ ሁሉ ፊት፣ ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ። (መዝሙር 116፥12-14)

“ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ ለእግዚአብሔር መክፈል” የሚለውን ቋንቋ መጠቀሙ ግርታን ይጭርብኛል። መልሶ መክፈል የሚለው ሐሳብ ጸጋን ልክ ቤትን በብድር እንደ መግዛት ያስመስለዋል። ይህ ዐይነት ብድር ጠቃሚ ይመስላል፤ ሆኖም ግን የግድ መልሰን መክፈል ይጥበቅብናል።

ጳውሎስ በሐዋርያት ሥራ 17፥25 ላይ እግዚአብሔር፣ “ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም” ብሏል። በሌላ አነጋገር፣ እግዚአብሔር አስቀድሞ ያልሰጠንን፣ መልሰን ለእርሱ መስጠት አንችልም።

ይህንን እንደገና በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10 ላይ እናያለን፦ “ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ አሁን የሆንሁትን ሆኛለሁ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋ ከንቱ አልሆነም፤ እንዲያውም ከሁሉም በላይ በትጋት ሠርቻለሁ፤ ዳሩ ግን እኔ ሳልሆን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው።” ስለዚህ የትኛውም ሥራችን ለእግዚአብሔር ክፍያ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም ሥራው ራሱ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። ለእግዚአብሔር በምናደርገው እያንዳንዱ ተግባር ውስጥ፣ የበለጠ የጸጋ ባለ ዕዳ እንሆናለን።

ስለዚህ በመዝሙር 116 ላይ ስእለትን እንደ ዕዳ ክፍያ ከማሰብ አደጋ ነፃ የሚያደርገው እውነት፣ “ክፍያው” በእውነቱ ተራ ክፍያ ሳይሆን፣ የማያቋርጠውን የእግዚአብሔር ጸጋ የሚያጎላ ሌላ የመቀበል ተግባር መሆኑ ነው። የእግዚአብሔርን እንጂ የእኛን ባለጠግነት አያጎላም።

ዘማሪው፣ “ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር ምን ልክፈለው?” ለሚለው ለራሱ ጥያቄ የሰጠው መልስ ይህ ነው፦ “የመዳንን ጽዋ አነሣለሁ፤ የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ።” በሌላ አነጋገር፣ ጽዋውን እንዲሞላ ጌታን እጠራለሁ። ለጌታ መክፈል ማለት የማያልቅ ቸርነቱ ጎልቶ እንዲታይ ከእርሱ እየተቀበሉ መቀጠል ማለት ነው።

የመዳንን ጽዋ ማንሣት የጌታን አጥጋቢ ማዳን መረከብን እና የበለጠ መጠባበቅን ያመለክታል። ይህን የምናውቀው በሚቀጥለው ሐረግ ምክንያት ነው፦ “የእግዚአብሔርንም ስም እጠራለሁ።” ለበለጠ እርዳታ ስሙን እጠራለሁ። ጥሪዬን በጸጋ ስለ መለሰልኝ ለእግዚአብሔር ምን አቀርባለሁ? መልሱ፦ እንደገና ስሙን እጠራለሁ። ምስጋናና መሥዋዕትን አንዳች ለማይጎድለው ለእግዚአብሔር እሰጣለሁ፤ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ሁሉ ጸጋው ለእኔ የተትረፈረፈ ነው።

ከዚያም ዘማሪው፣ በሦስተኛ ደረጃ “ስእለቴን ለእግዚአብሔር እፈጽማለሁ” ብሏል። ግን እንዴት ነው ስእለቱ የሚከፈለው? ይኽውም የመዳንን ጽዋ በማንሣት እና ጌታን በመጥራት ነው። ይህም ማለት፣ የተትረፈረፈ ጸጋ ሁልጊዜ በፊታችን እንዳለ የሚናገረውን የተስፋ ቃል በማመን ስእለቱ ይከፈላል።