እንዴት ንስሓ እንግባ | ጥር 28

ኀጢአታችንን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው። (1ኛ ዮሐንስ 1፥9)

ግልጽ ያልሆነ፣ እንዲያው በደፈናው ግን የማትረቡ ሰው መሆናችሁን በማሰብ የሚመጣ መጥፎ ስሜት እና በርግጥ በኀጢአታችሁ መወቀስ ተመሳሳይ ነገር አይደሉም። ርካሽ ወይም ቆሻሻ የመሆን ስሜት እና ንሰኀ መግባት አንድ አይደሉም።

ዛሬ ጠዋት መጸለይ ስጀምር፣ የአጽናፈ ዓለሙ ፈጣሪ የሆነውን እግዚአብሔርን ለማናገር የማይገባኝ እንደሆንኩ ተሰማኝ። ግልጽ ያልሆነ የአይገባኝም ስሜት ነበር። ስለዚህም ያንን ነገርኩት። ከዚያስ ግን?

ኃጢአቶቼን አንድ በአንድ መዘርዘር እስክጀምር ድረስ ምንም የተቀየረ ነገር አልነበረም። የዋጋ ቢስነት ስሜት፣ ኃጢአታችንን በዝርዝር አምኖ ወደ መቀበል ካመራ፣ ሊጠቅም ይችላል። እንዲያው በደፈናው ግን፣ “እኔ እኮ መጥፎ ሰው ነኝ” ብሎ ማሰብ ጥቅም የለውም።

አይገባኝም የሚለው ግልጽ ያልሆነ ስሜት፣ ግልጽ ወደ ሆነ፣ “ይህን ተላልፍያለሁ” ወደሚል ኑዛዜ መቀየር አለበት። የሠራነውን ኀጢአት ነቅሰን ካወጣን በኋላ ንሰሀ መግባት፣ ምሕረትን መጠየቅ እና በወንጌል እውነት ያንን ኀጢአት ድባቅ ልንመታው እንችላለን።

ስለዚህ ብዙ ጊዜ የምተላለፋቸውን ትዕዛዛት ማሰብ ጀመርኩ። ወደ ዐሳቤ የመጡት እነዚህ ነበሩ።

  • ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ፦ 95% ሳይሆን 100%። (ማቴዎስ 22፥37)
  • ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ፦ ጥሩ ነገሮች ለራሳችሁ እንዲሆኑ በምትጓጉት ልክ፣ ለሌሎችም መልካምን ሁሉ ተመኙ። (ማቴዎስ 22፥39)
  • ማንኛውንም ነገር ሳታጉረመርሙ አድርጉ፦ በውስጥም ሆነ በውጪ – ምንም ሳታጉረመርሙ። (ፊልጵስዩስ 2፥14)
  • እናንተ ላይ ሸክም ሆነው እንዳይጎትቷችሁ፣ የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት። (1 ጴጥሮስ 5፥7)
  • ሌሎችን የሚያንጽና ጸጋን የተሞላ ንግግር ብቻ ተናገሩ፣ በተለይ ደግሞ ለሚቀርቧችሁ ወገኖች። (ኤፌሶን 4፥29)
  • ዘመኑን ዋጁ። በማይረባ ድርጊት ደቂቃዎቻችሁን አታባክኑ። (ኤፌሶን 5፥16)

ይህ ሁሉ መተላለፍ። ታላቅ ቅዱስ ነኝ ብዬ ማሰቤን ገደል ከተተው። አሁን ብትንትኔ ወጥቷል።

ይህ ከተዳፈነው የመጥፎነት ስሜት እጅግ የባሰ ነው። አሁን ግን ጠላቱ ግልፅ ሆኖ ይታያል። ኃጢአቶቹ ተለቅመዋል። ከተሰወሩበት ወጥተዋል። ለተሰማኝ መጥፎ ስሜት እያጉረመረምኩ ብቻ አይደለም። ክርስቶስ ያዘዘኝን ስላላደረግሁ ይቅርታን እየጠየቅሁ ነው።

አሁን ተሰብሬአለሁ፣ በኃጢአቴም ተቆጥቻለሁ። ልገድለው እፈልጋለሁ። ራሴን ሳይሆን፣ ኃጢአቴን የምጠላ እና የምገድል ሰው ነኝ። “ምድራዊ ምኞቶቻችሁን ግደሉ” (ቆላስይስ 3፥5)፣ “ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ግደሉ” (ሮሜ 8፥13)። መኖር እፈልጋለሁ፤ ለዚያም እገለዋለሁ። እኔ የኃጢአቴ ገዳይ ነኝ።

በዚህ ትግል ውስጥ ሆኜ፣ “ኃጢአታችንን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን፣ ከዐመፃ ሁሉ ሊያነጻን እርሱ ታማኝና ጻድቅ ነው” የሚለውን ተስፋ ሳደምጥ፣ ሰላም በውስጤ ይሰፍናል (1ኛ ዮሐንስ 1፥9)።

አሁን ጸሎት የሚቻል ይሆንልኛል። ትክክለኛ እና ኃይለኛ እንደሆነም ይሰማኛል።