በአሰቃቂ መከራ ውስጥ እያለን በእግዚአብሔር መልካምነት እና ሉዓላዊ ጥበብ ብናምን፣ ስሜታችን ምን የሚሆን ይመስላችኋል?
ይህን ጥያቄ ያነሣሁት ለሁለት ምክንያቶች ነው።
የመጀመሪያው፣ እግዚአብሔር ለስሜታችን ያለው ፈቃድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጠ መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ በእግዚአብሔር ሕዝብ ልብ ውስጥ ዛሬ ላይ እየሆነ የማየው ነገር ነው። እነዚህ ሁለቱ አብዛኛውን ጊዜ ተመሳሳይ አይደሉም። ታዲያ አንዱ ዓላማዬ፣ ዛሬ ላይ ያሉ ቅዱሳን እግዚአብሔር ለስሜታችን ያለውን ግብ እንዲለማመዱ መርዳት ነው።
ለምሳሌ እንዲሆን ቅርብ ጊዜ ያነበብኩትን ላካፍላችሁ።
በአስከፊ ስደት መታደስ?
ራእይ 6 ላይ ዮሐንስ፣ “ስለ እግዚአብሔር ቃል … የታረዱትን ሰዎች ነፍሶች” ያያል። እነዚህ ሰዎች ለኢየሱስ ሰማዕት የሆኑ በሰማይ ያሉ ሰዎች ናቸው። “እነርሱም በታላቅ ድምፅ፣ ‘ሁሉን የምትገዛ፣ ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ፤ እስከ መቼ አትፈርድም? እስከ መቼስ ደማችንን በምድር በሚኖሩት ላይ አትበቀልም?’ አሉ” (ቁጥር 10)።
የሚገኙት በሰማይ “ፍጹምነትን ካገኙ ከጻድቃን መንፈሶች” ዘንድ ስለሆነ፣ ይህ ጩኸታቸው ኀጢአት ያለበት ነው ለማለት ባንቸኩል መልካም ነው (ዕብራውያን 12፥23)። ነገር ግን እግዚአብሔር ስሜታቸውን ከጥድፊያ ይልቅ ወደ ሌላ የልብ ልምምድ ይመራዋል።
ሰማዕታቱንም “ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ” ይነግራቸዋል። ይህ መታገስ (anapauō) የሚለው ቃል ስሜትን የሚያድስ እና ሰላምን የሚሰጥ ቃል ነው። በሚከተሉት ምሳሌዎች ውስጥ የዚህን ቃል አንድምታ መረዳት እንችላለን።
“እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ” (ማቴዎስ 11፥28)። “የእኔንም የእናንተንም መንፈስ አሳርፈዋልና” (1ኛ ቆሮንቶስ 16፥18)። “ወንድሜ ሆይ፤ የቅዱሳንን ልብ ስላሳረፍህ ከፍቅርህ ታላቅ ደስታና መጽናናት አግኝቻለሁ” (ፊልሞና 1፥7)። “ወንድሜ ሆይ፤ በጌታ እንድትጠቅመኝ እፈልጋለሁ፤ በክርስቶስ ልቤን አሳርፍልኝ” (ፊልሞና 1፥20)።
ይሁን እንጂ ስሜትን የሚንጠው ነገር ይህ ነው፦
ምድር ላይ ስላለው አስከፊ ስደት በግልጽ እንዲያውቁ ተደርገው ነበር። “ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪሞላ ድረስ” እንዲያርፉና ስሜታቸው እንዲታደስ ነበር የተነገራቸው።
ይህ ስሜትን የሚያናውጥ ነገር ነው።
የዕረፍታቸው ቁልፍ ምስጢር
አራት ነገሮችን ልብ በሉ፦
- እንዲያርፉና ስሜታቸው እንዲታደስ ተነግሯቸው ነበር።
- እነርሱ በዕረፍት ላይ ሳሉ፣ ሰዎች ግን እየተገደሉ — ሲከፋም እየተሰየፉ —እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር (ራእይ 20፥4)።
- ደግሞም እነርሱ በዕረፍት ላይ ሳሉ፣ እየሞቱ ያሉት ሰዎች ወንድሞቻቸው እንደሆኑ ተነግሯቸው ነበር።
- እንዲሁም የሟቾች ቁጥር በእግዚአብሔር የተወሰነ እንደሆነም ተነግሯቸው ነበር።
ስለዚህ፣ ተግባራዊ እንዲሁም ስሜትን ከሚነካ እውነተኛ ጥያቄ ጋር እንጋፈጣለን፦ እነዚህ ቅዱሳን ወንድሞቻቸው በአሰቃቂ ሁኔታ እየተገደሉ እያለ እንኳ፣ በፍጥነት እንዲሆን ከሚገልጉት የበቀል ስሜታቸው ወጥተው እንዲያርፉ እግዚአብሔር ይጠብቅባቸዋል ማለት ነው?
አዎን ይጠብቅባቸዋል። እግዚአብሔር የሚቻል እና ትክክል እንደሆነ ባያስብ ኖሮ እነዚህን ቅዱሳን እንዲያርፉ ባልነገራቸው ነበር።
የማረፋቸው ቁልፍ ምስጢር፣ በራዕይ 6፥11 ላይ በምናየው የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጥበብ እና መልካምነት ላይ የተመሰረተ ነው — ገና የሚገደሉ፣ ቍጥራቸው በእግዚአብሔር የተወሰነ ሰማዕታት አሉ። “ወደ ፊት እንደ እነርሱ የሚገደሉ የአገልጋይ ባልንጀሮቻቸውና ወንድሞቻቸው ቍጥር እስኪሞላ ድረስ ጥቂት ጊዜ እንዲታገሡ ተነገራቸው።”
በእግዚአብሔር ጥበብ እና መልካምነት ውስጥ ያለ ጥልቅ የነፍስ ዕረፍት
ታዲያ ይህ ማለት በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጥበብ እና መልካምነት ላይ ያለን ጥልቅ መታመን ለአሰቃቂ ሁኔታዎች የሚኖረንን ስሜታዊ ምላሽ ከመሰረቱ ይለውጠዋል ማለት ነው። በአስከፊ መከራ ውስጥ እንኳ ሆነን በእግዚአብሔር ያረፈች ነፍስ እንዲኖረን ከሰማይ አቅም ተሰጥቶናል።
ይህ ማለት ምንም የማይጨንቀን እንሆናለን ማለት አይደለም። ርኅራኄ ማጣት ወይም ግድ የለሽነትም አይደለም። እንዲሁም የእንባ ድርቀትም አይደለም። ነገር ግን ዕረፍት ነው። በኢየሱስ ላይ የተደገፈ ጥዑም ዕረፍት ነው።
በኢየሱስ ላይ ለማረፍ
ነፍሴ ሄዳ ብትደገፍ
እንዲች ብዬ አልከዳትም
ለጠላቷ አልተዋትም
የራሳችንንም ጨምሮ — የመከራንና የስደትን አስከፊነት እያወቅን እንኳ፣ ጥልቅ የሆነ የስሜት ዕረፍት — ጥልቅ የሆነ የነፍስ እፎይታ ግን አለን።
በጆን ፓይፐር