“ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ በሙሉ ልብ አገልግሉ፤ ምክንያቱም፣ ባሪያም ሆነ ነጻ ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችሁ።” (ኤፌሶን 6፥7-8)
ከሥራችሁ ጋር በተያያዘ እነዚህን አምስት ነገሮች ከኤፌሶን 6፥7-8 እንመልከት።
- አምላክ ተኮር ወደ ሆነ ኑሮ መጠራት
መኖር ከለመድነው አንጻር ይህ አስገራሚ ነው። ጳውሎስ ሥራችን ሁሉ ለክርስቶስ እንጂ ለየትኛውም ዓይነት አለቃ እንዳይሆን ይነግረናል። በሙሉ ልብ “ሰውን ሳይሆን ጌታን እንደምታገለግሉ ሆናችሁ” አገልግሉ።
ይህ ማለት በምንሠራው ሁሉ ጌታን እናስበዋለን ማለት ነው። ጌታ ለምን ይህን እንድሠራ ፈለገ? እንዴትስ እንድሠራው ይፈልጋል? መቼስ እንዳደርገው ይፈልጋል? ይህንንስ እንዳደርግ ጌታ ይረዳኝ ይሆን? ደግሞስ ይህ ለጌታ ክብር ምን አስተዋዕፆ አለው? ብለን እንጠይቃለን። በሌላ አነጋገር፣ ክርስቲያን መሆን ማለት አምላክ ተኮር የሆነ ኑሮን መኖር እና ሥራን መሥራት ማለት ነው።
- መልካም ሰው ለመሆን መጠራት
አምላክ ተኮር የሆነ ኑሮ ማለት መልካም መሆንና መልካምን ማድረግ ማለት ነው። ጳውሎስ “በሙሉ ልብ … ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ” ይላል። ኢየሱስም ብርሃናችንን ስናበራ ሰዎች ̔መልካም ሥራችንን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችንን እንደሚያከብሩ ነግሮናል (ማቴዎስ 5፥16)
- ለማይመቹ ምድራዊ አለቆች መልካም ሥራን የመሥራት አቅም
የጳውሎስ ዓላማ፣ አምላክን ማዕከላዊ ባደረገ ተነሳሽነት፣ ለማይመቹ አለቆች መልካምን ለማድረግ ክርስቲያኖችን ማበረታታት ነው። አለቃችሁ የማያናግራችሁ ወይም ያለማቋረጥ የሚተቻችሁ ሆኖ እንዴት ነው መልካምን ማድረግ የምትችሉት? የጳውሎስ መልስ እንዲህ የሚል ነው፦ የሥራ አለቃችሁን እንደ ዋና የበላይ ኅላፊ ማየት አቁማችሁ፣ ለአምላካችሁ መሥራት ጀምሩ። ይህንንም ምድራዊ አለቃችሁ በሚሰጣችሁ ሥራዎች ሁሉ ማድረግ ይገባችኋል።
- መልካም ሥራ በከንቱ እንዳይደረግ ማወቅ
እስከዛሬ ከተነገሩ ንግግሮች ሁሉ እጅግ አስደናቂ የሆነው ንግግር፣ “ሰው ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ እንደሚቀበል ታውቃላችው?” የሚለው ነው። ይህ በጣም የሚገርም ነው። “ለሚያደርገው በጎ ነገር ሁሉ።” የምታደርጉት እያንዳንዱ ጥቃቅን ነገር በጌታ ዘንድ የሚታይ፣ ዋጋ ያለውና የሚያሸልም ነው።
ለሁሉም ይከፍላችኋል። ነገር ግን የሚከፍላችሁ እርሱ ባለ ዕዳ ሆኖ የሠራችሁበትንና የሚገባችሁን አይደለም። እናንተን ጨምሮ ፍጥረተ ዓለሙ ሁሉ የእርሱ ነው። እርሱ የማንም ባለ ዕዳ አይደለም። ነገር ግን በቸርነቱ በእምነት ላደረግናቸው መልካም ሥራዎች ሊሸልመን ስለመረጠ ነው።
- በምድር የበታች መሆን በሰማይ ላለው ታላቅ ሽልማት እንቅፋት አለመሆኑን ማወቅ
“ባሪያም ሆነ ነፃ ሰው” – ለምታደርጉት በጎ ነገር ሁሉ ሽልማቱን ከጌታ ትቀበላላችሁ። የሥራ አለቃችሁ እንደ ተራ አገልጋይ ወይም እንደ ባሪያ ሊያስባችሁ ይችላል። ይባሱንም መኖራችሁን ላያውቅም ይችላል። ይህ ግን ምንም ለውጥ አያመጣም። ጌታ ያውቃችኋልና። በመጨረሻም የትኛውም የታመነ አገልግሎት በከንቱ እንደማይሆን እንወቅ።