ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር የሚቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ለመቀደስም ፈልጉ፤ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም። (ዕብራውያን 12፥14)
ተግባራዊ በሆነ የቅድስና ኑሮ የማይኖር ሰው ጌታን ከማየት ይከለከላል። የብዙዎች አኗኗር ግን ይህንን ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም።
ያልተቀደሰ ሕይወትን የሚኖሩ፣ “ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ” የሚለውን የኢየሱስን አስፈሪ ቃል የሚሰሙ፣ ክርስቲያን ነን ባዮች አሉ (ማቴዎስ 7፥23)። ጳውሎስ አማኝ ነን ለሚሉ ሰዎች “እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁ” እንደሚላቸው እናነብባለን (ሮሜ 8፥13)።
ስለዚህ፣ ያለ ቅድስና ማንም ጌታን ማየት አይችልም። ለዚህ ደግሞ በሚያስፈልገን ጊዜ በሚሰጠን ጸጋ ላይ በመታመን፣ ለቅድስና መታገልን መማር ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው።
ወደ ሞት የሚመራን እና ክፉኛ የሚጎዳን ሌላ የተሳሳተ የቅድስና መንገድ አለ። ጳውሎስ፣ ኀይልን በሚሰጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ባለን እምነት ካልሆነ በቀር በሌላ በማንኛውም መንገድ እግዚአብሔርን ለማገልገል እንዳንሞክር ያስጠነቅቀናል። እግዚአብሔር፣ “ለሰዎች ሁሉ ሕይወትንና እስትንፋስን እንዲሁም ሌላውንም ነገር ሁሉ የሚሰጥ ስለ ሆነ፣ የሚጐድለው ነገር ባለመኖሩ በሰው እጅ አይገለገልም” (ሐዋርያት ሥራ 17፥25)። እግዚአብሔርን እንደ ትልቁ ሐብታችንና የአገልግሎታችን ኃይል አድርጎ የማይታመን ማንኛውም የአገልግሎት ጥረት፣ እግዚአብሔርን እንደ ስጡኝ ባይ አረማዊ አምላክ በመቁጠር ያዋርደዋል።
ከዚህ በተቃራኒ ያለውን፣ በራስ ከመተማመን ይልቅ በእግዚአብሔር ታምኖ እርሱን ማገልገልን ጴጥሮስ እንዲህ ይገልጸዋል፦ “የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው” (1ኛ ጴጥሮስ 4፥11)። ጳውሎስም፣ “ክርስቶስ በእኔ ሆኖ ከፈጸመው በቀር ሌላ ነገር ለመናገር አልደፍርም” በማለት ተናግሯል (ሮሜ 15፥18፤ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፥10)።
እግዚአብሔር በእኛ ሊሰራ ያቀደውን “በጎ ሥራ ሁሉ” መሥራት የሚያስችለን ጸጋ በእያንዳንዱ ቅጽበት ይሰጠናል። “ሁልጊዜ በሁሉ ነገር የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ አግኝታችሁ ለበጎ ሥራ ሁሉ እንድትተርፉ፣ እግዚአብሔር ጸጋን ሁሉ ሊያበዛላችሁ ይችላል” (2ኛ ቆሮንቶስ 9፥8)።
በጎ ሥራን ለመስራት የሚደረገው ትግል እግዚአብሔርን ለማመን የሚደረግ ትግል ነው። በሚያስፈልገን ጊዜ ሁሉ ጸጋን እንደሚሰጠን የገባውን ቃል ለማመን ከነፍሳችን ጋር የምናደርገው ትንቅንቅ ነው።