“እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአእምሯችን በላይ ታላቅ ነው! የዘመኑም ቍጥር ከመታወቅ ያልፋል።” (ኢዮብ 36፥26)
እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ማወቅ አይቻልም።
የመላው ዓለም ውዱ እና አስፈላጊው ነገር እግዚአብሔር ነው። ነገሮችን ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፣ ያላቸውን መልክ፣ ይዘትና ዋጋ የሰጣቸው እርሱ ነው።
ፍጥረታት ሁሉ ያላቸው ጥንካሬ፣ ብልሃት፣ ችሎታ፣ ወይም ውበት የመጣው ከእርሱ ነው። በየትኛውም ችሎታ መለኪያ ቢመዘን፣ በዚህ ምድር ካሉ እጅግ ምርጥ እና ጀግና ሰዎች ሁሉ ሊለካ በማይችል መልኩ እጅግ የላቀ ነው።
እግዚአብሔር ወሰን አልባ ስለሆነ፣ ሊመረመርና ተዘርዝሮ ሊያልቅ በማይችል ሁኔታ ማራኪ ነው። ስለዚህም እግዚአብሔር በፍጹም ሊሰለች አይችልም። ከእርሱ የሚመነጩ ጥበብን የተሞሉና አስደናቂ ድርጊቶች ሁሉ ልክ እንደ እሳተ ገሞራ ኀይለኛና ነውጥን ፈጣሪ ናቸው።
የደስታ ሁሉ ምንጭ ስለሆነ፣ የሚሰጠው ደስታ ፍጹም እና ሙሉ ነው። እግዚአብሔርን የምናውቀው እንደዚህ ካልሆነ ወይ ሞተናል፣ ወይ አይናችን ታውሯል፣ ወይ በቁማችን ተኝተናል።
ታዲያ እግዚአብሔር እንደዚህ አሰደናቂ ሆኖ ሳለ፣ በዚህ ዓለም ግን እርሱን ለማወቅ የሚደረገው ጥረት እጅግ አናሳ መሆኑ ይገርማል።
የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤታችሁ ለአንድ ወር ቢቀመጥና እናንተ ግን ከአልፎ አልፎ ሰላምታ ውጪ ችላ እንደማለት ነው። ወይም በመንኩራኩር ወደ ሕዋ መጥቃችሁ በፀሐይ እና በህዋ ዙሪያ ለሰዓታት በብርሃን ፍጥነት እየበረራችሁ፣ በመስኮት በውጭ ያለውን አስደናቂ ትዕይንት ከመመልከት ይልቅ ፌስቡክ እንደ መጠቀም ነው። ወይም ደግሞ ምርጥ ተዋንያን፣ ድምጻዊያን፣ አትሌቶች፣ የፈጠራ ባለቤቶች፣ እንዲሁም ምሁራን ግኝቶቻቸውን እና ሥራዎቻቸውን በሚያቀርቡበት ዝግጅት ላይ ተጋብዛችሁ፣ እናንተ ግን እሁድን በኢ.ቢ.ኤስ ለማየት በቤታችሁ እንደ መቅረት ነው። ፍጻሜና ወሰን የሌለው ግሩም አምላካችን ልባችንን ወደ እርሱ እንዲያዘነብልልን እና እርሱን እንድንሻ፣ ደግሞም አይኖቻችንን ከፍቶ በምንችለው ልክ እርሱን ማየት እንችል ዘንድ እንጸልይ።