በየትኛውም ሁኔታ ባለኝ ነገር መርካት እችላለሁ | ሰኔ 26

ይህን የምለው ስለ ቸገረኝ አይደለም፤ ምክንያቱም በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ያለኝ ይበቃኛል ማለትን፣ ማጣትን ዐውቀዋለሁ፤ ማግኘትንም ዐውቀዋለሁ። ብጠግብም ሆነ ብራብ፣ ባገኝም ሆነ ባጣ፣ በማንኛውም ሆነ በየትኛውም ሁኔታ ያለኝ ይበቃኛል የማለትን ምስጢር ተምሬአለሁ። ኀይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ። (ፊልጵስዩስ 4፥ 11–13)

እግዚአብሔር ለጳውሎስ በየዕለቱ የሚሰጠው ጸጋ በጥጋብ እና በረሃብ፣ በብልጽግና እና በመከራ፣ እንዲሁም በማግኘት እና በማጣት እንዲያልፍ አስችሎታል።

“ሁሉንም ማድረግ እችላለሁ” ማለት ቀላል ነገሮችን ብቻ ሳይሆን፣ “ሁሉንም ነገር” ማለት ነው። “ሁሉን” ማለት “በክርስቶስ በኩል መራብንም ሆነ መከራን መቀበልን፣ እንዲሁም መቸገርን እችላለሁ” ማለት ነው። ታዲያ ይህ እውነት በፊልጵስዩስ 4፥19 ላይ የሚገኘውን አስደናቂ የተስፋ ቃል ልዩ ትርጉም ይሰጠዋል፦ “አምላኬም እንደ ታላቅ ባለጠግነቱ መጠን የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ በክርስቶስ ኢየሱስ ይሞላባችኋል።”

ፊልጵስዩስ 4፥11-12 አንጻር “የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ” ማለት ምን ማለት ነው? “የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ” ማለት “እግዚአብሔርን ለሚያከብር እርካታ የሚያስፈልጋችሁ ሁሉ” ብለን ልንረዳው እንችላለን። ይህም የረሃብ እና የችግር ጊዜያትን ሊያካትት ይችላል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ያለው ፍቅር በእግዚአብሔር ላይ ካለው እርካታ የመነጨ ነው። ይህም እርካታው የሚመነጨው፣ በማግኘትም ሆነ በማጣት ወቅት የሚያስፈልገውን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንደሚያገኝ ካለው ጽኑ እምነት ነው።

ስግብግብነት የእምነት ፍጹም ተቃራኒ የሆነው ለዚህ ነው። በክርስቶስ ያለንን እርካታ የማጣታችን ምልክት ነው። በዚህም ምክንያት በእግዚአብሔር መገኘት ብቻ የሚረካውን የልባችንን መሻት ለማርካት፣ ሌሎች ነገሮችን መመኘት እንጀምራለን። ይህ ከስግብግብነት ጋር የሚደረገው ውጊያ፣ እግዚአብሔር በሚያስፈልገን ጊዜ ጸጋን እንደሚሰጠን የገባውን ቃል ካለማመን ጋር የሚደረግ ውጊያ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።  

ይህ ደግሞ በዕብራውያን 13፥5 ላይ ግልጽ ሆኖ ተቀምጧል። የዕብራውያን ጸሐፊ ገንዘብን ከመውደድ እና ከስግብግብነት ነፃ እንወጣ ዘንድ በእግዚአብሔር መርካት እንደሚገባን ሲሞግት ተመልከቱ፦ “ራሳችሁን ከፍቅረ ንዋይ ጠብቁ፤ ባላችሁ ነገር ረክታችሁ ኑሩ፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር፣ ‘ከቶ አልተውህም፤ በፍጹም አልጥልህም’ ብሏል።” “በፍጹም አልተውህም” የሚለውን የተስፋ ቃል ማመን፣ ስግብግብነትን ጨምሮ እግዚአብሔርን የማያከብርን የትኛውንም የምኞት ኃይል ሁሉ ይሰብራል።

በልባችን ውስጥ ቅንጣት እንኳ የምታህል የስግብግብነት እና የራስ ወዳድነት ስሜት ቢሰማን፣ የዚህን እምነት የጦር ዕቃ ተጠቅመን በሙሉ ኃይላችን ልንዋጋው ይገባናል።