ሐሳቦች መዘዝ አላቸው | ግንቦት 15

የዚህ ትእዛዝ ዐላማ … ፍቅር ነው። (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥5)

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ “አውሽዊትዝ” እና “ዳኻው” በሚባሉ የናዚ ማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ ቪክተር ፍራንክል የተባለ ሰው ታስሮ ነበር። ቪክተር አይሁዳዊ የኒውሮሎጂ እና ሥነ-አእምሮ ፕሮፌሰር ነበር። ከስምንት ሚሊየን ኮፒ በላይ በተሸጠው “Man’s Search for Meaning” በተሰኘው መፅሐፉም እውቅናን ማትረፍ ችሏል።

በዚህ መጽሐፉ ውስጥም ሎጎቴራፒ ስለተባለው ፍልስፍናው ያብራራል። ይህ ፍልስፍናውም “የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት፣ የሕይወትን ትርጉም ፈልጎ ማግኘት ነው” የሚል ነበር። በናዚ ማጎሪያ ጣቢያዎች ውስጥ ካያቸው በርካታ አሰቃቂ ክስተቶች የተረዳው ነገር፣ የሰው ልጅ “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ መልስን ካገኘ፣ “እንዴት?” የሚለውን ጥያቄ መቋቋም እንደማይከብደው ነው። የሰው ልጅ በምንም ነገር ሲያልፍ፣ ምክንያት እስካለው ድረስ ምንም ነገርን ታግሶ ማለፍ ይችላል። መታገስ የመቻል አቅም እንዳለው ነው። ከጻፋቸው ነገሮች መካከል ልቤን የነካው አንዱ ይህ ነው፦

አይሁድን ለመጨፍጨፍ ናዚ የተጠቀመባቸው፣ በ”አውሽዊትዝ”፣ “ትሬብሊንካ” እና “ማይዳኔክ” የሚገኙት የማቃጠያ የጋዝ ክፍሎች በዋነኛነት የተዘጋጁት፣ በአንድ የመንግስት ሚንስቴር መሥሪያ ቤት ወይም በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን ነው ብዬ አላምንም። ይልቁንም በሳይንቲስቶች እና በፈላስፎች መማሪያ ክፍሎች እና ጠረጴዛዎች ላይ የታሰቡ መሆናቸውን አልጠራጠርም።

(“Victor Frankl at Ninety: An Interview,” in First Things, April 1995, p. 41.)

በሌላ አነጋገር፣ ሐሳቦች — የሚያለሙም ይሁኑ የሚያጠፉ — መዘዝ አላቸው። የሰዎች ባህርይም —  ጥሩም ሆኑ መጥፎ — ያለ ምክኒያት ግን አይመጡም። በአእምሮአችን ውስጥ ሥር ከሰደዱ ጥሩም ሆነ መጥፎ አስተሳሰቦች የሚመነጩ ናቸው።

መፅሐፍ ቅዱስ፣ “ሐሳቦች መዘዝ አላቸው” የሚለውን እውነት ለማስረዳት እንዲህ ይላል፦ “ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና” (ሮሜ 15፥4)። በቃሉ ውስጥ የተፃፉት ነገሮች የወደፊት ተስፋን ይወልዳሉ።

በድጋሚ ጳውሎስ እንዲህ ይላል፦ “የዚህ ትእዛዝ ዐላማ … ፍቅር ነው” (1ኛ ጢሞቴዎስ 1፥5)። በትዕዛዝ የሚፈፀሙ ሐሳቦች ፍቅርን ይወልዳሉ።

ተስፋ እና ፍቅር ዝም ብለው አይመጡም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጡ ሐሳቦች እና እውነታዎች ይወለዳሉ እንጂ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ሐሳቦች መዘዝ እንዳላቸው” የሚያሳይበት ሌላው መንገድ፦ “ስለዚህ፣ ስለ” ወይም “እንግዲህ” የሚለውን ቃል በመጠቀም ነው። ይህ ቃል ምክንያትን ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥም ከሺህ በላይ ጊዜ ተጠቅሷል። “ስለዚህ” ወይም “እንግዲህ” የሚለው ቃል፣ ቀጥሎ የሚመጣው ጉዳይ ከሆነ ቦታ ነው የመጣው ማለት ነው። የሆነ የተመሠረተበት ነገር አለ። ለምሳሌ፣ “እንግዲህ በእምነት ስለ ጸደቅን፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም አለን” (ሮሜ 5፥1)፣ ወይም ደግሞ፣ “ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም” (ሮሜ 8፥1)፣ በተጨማሪም፣ “ስለዚህ ለነገ በማሰብ አትጨነቁ” (ማቴዎስ 6፥34)።

ይህ ውድ ቃል በሚያመለክታቸው በእነዚህ ታላላቅ እውነታዎች ውስጥ መኖር ከፈለግን፣ ከዚህ ቃል በፊት የነበሩትን ሐሳቦችና እውነታዎች መያዝ አለብን። አትርሱ፣ ሐሳቦች ሁሉ የሆነ መዘዝ እና ውጤት አላቸው። ስለዚህ፣ ሐሳቦቻችንን በሙሉ በእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ሥር እናስገዛ።