የሥጋ ምኞትን ካልተዋጋችሁት | ሐምሌ 26

ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት እንድትርቁ እለምናችኋለሁ” (1ኛ ጴጥሮስ 2፥11)።

በአንድ ወቅት፣ በአመንዝራነት ሕይወት ውስጥ ያለ አንድን ሰው መገሰጽ ነበረብኝ። ሁኔታውን ለመረዳት ሞከርኩ፣ ወደ ሚስቱ እንዲመለስም ተማጸንኩት። ከዚያም ኢየሱስ የተናገረውን አስታወስሁት፦ ‘ይህን ኃጢአት ዓይንህን ለማውጣት ፈቃደኛ እስክትሆን ድረስ ጨክነህ ካልተዋጋህ፣ ሲኦል ትገባለህ፤ በዚያም ለዘላለም ትሠቃያለህ’ ብሎሃል አልኩት።

ክርስቲያን ነኝ እንደሚል ሰው በሕይወቱ እንደዚህ ዐይነት ነገር ሰምቶ የማያውቅ ይመስል ተደናግጦ አያየኝ፣ “አንድ ሰው መዳኑን ሊያጣ ይችላል ብለህ ታስባለህ ማለት ነው?” አለኝ።

በአገልግሎት ዘመኔ በተደጋጋሚ የተማርኩት አንድ እውነት አለ። በርካታ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች መዳንን ከዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ነጥለው ይመለከቱታል። መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ማስጠንቀቂያዎች ችላም ይላሉ። ከዚያም አልፈው፣ አንድ ሰው ክርስቲያን ነኝ ካለ፣ በቋሚነት ኃጢአትን ቢለማመድ እንኳ የቃሉ ማስጠንቀቂያዎች የማይመለከቱት ይመስላቸዋል። ይህ ዐይነቱ የክርስትና ሕይወት ምልከታ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደ ዘላለም ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ እያታለለ እየጎተታቸው መሆኑ እጅግ ያሳዝናል (ማቴዎስ 7፥13)።

ኢየሱስ ክርስቶስ በግልጽ የነገረን ነገር ከሥጋዊ ምኞቶቻችን እና ከዝሙታዊ አስተሳሰቦቻችን ጋር ካልተዋጋን መንግሥተ ሰማይን በፍጹም ልናይ እንደማንችል ነው። “ቀኝ ዓይንህ የኀጢአት ሰበብ ቢሆንብህ፣ አውጥተህ ወዲያ ጣለው፤ ሰውነትህ በሙሉ ወደ ገሃነም ከሚጣል ከሰውነትህ አንዱን ክፍል ብታጣ ይሻልሃል” (ማቴዎስ 5፥29)። ይህ ማለት እውነተኛ ክርስቲያኖች ከኀጢአት ጋር በሚያደርጉት እያንዳንዱ ተጋድሎ ያሸንፋሉ እያለ አይደለም። ዋናው ጉዳይ ለመታገል እና ሥጋን ለመግደል መቁረጣችን ነው እንጂ እንከን በሌለው ሁኔታ በየዕለቱ ይሳካልናል የሚልም አይደለም። ከኃጢአት ጋር እርቅን አንፈጥርም፣ በሰላምም አንኖርም፤ ይልቁንም ዕለት ዕለት ጦርነት እናውጃለን፣ እንዋጋለን።

የዚህ ጉዳይ አሳሳቢነት ከየትኛውም ዓለም ላይ ከተደነቀረ ስጋት በሺህ ዕጥፍ ይበልጣል። ዓለም ሁሉ በኒውክሌር ፍንዳታ የመጥፋት ሥጋት ሊኖርባት ይችላል፣ አሸባሪዎችም የምንኖርበትን ከተማ በፈንጂዎች ሊያጠቁ ይችሉ ይሆናል፣ የዓለም ሙቀት መጨመር የበረዶ ግግርን ሁሉ አቅልጦ ዓለም ልትሰጥም ትችላለች፤ እንደ ኤድስ ዓይነትም በሽታ ሕዝቦችን ጠራርጎ ሊፈጅ ይችላል። የዝሙት እና የአመንዝራነት ኀጢአት ውጤት ግን ከዚህ ሁሉ ይብሳል። እነዚህ ሁሉ አደጋዎች ሰውነትን ብቻ የሚገድሉ ናቸው። ሥጋዊ ምኞቶቻችንን ካልተዋጋን ግን ነፍሳችንን ለዘላለም እናጣለን። መመለሻም የለንም።

ጴጥሮስ የሥጋ ምኞት ነፍሳችን ላይ ጦርነትን እንደከፈተ ይነግረናል (1ኛ ጴጥሮስ 2፥11)። የዚህ ጦርነት አደጋ ከየትኛውም የዓለም ጦርነት ወይም ሽብርተኝነት ስጋት እጅግ የላቀ ነው። ሐዋርያው ​​ጳውሎስ “ዝሙትን፣ ርኩሰትን፣ ፍትወትን፣ ክፉ ምኞትን እና መጎምጀትን” ከዘረዘረ በኋላ “በእነዚህም ምክንያት የእግዚአብሔር ቍጣ ይመጣል” ሲል ያስጠነቅቀናል (ቆላስይስ 3፥5-6)። የእግዚአብሔርም ቁጣ በዓለም ላይ ካሉት የዓለም ሕዝቦች ሁሉ ቁጣ ይልቅ እጅግ የሚያስፈራ እና የሚያጠፋ ነው።

በዚህ ጉዳይ ቀልዱን ሁሉ ትተን፣ የገዛ ነፍሳችን እና የሌሎችም ነፍስ ሸክም እንዲከብድብን እና ይህንን ትግል በትጋት በመዋጋት እንድንቀጥል እግዚአብሔር ጸጋውን ሁሉ ያብዛልን!