አለማወቅ ከእውነተኛ መንፈሳዊነት ያጎድላል | መጋቢት 23

በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኀይል ሰጥቶናል። (2ኛ ጴጥሮስ 1፥3)

መጽሐፍ ቅዱስ ለዕውቀት የሚሰጠው ቦታ ይገርመኛል።

በድጋሚ 2ኛ ጴጥሮስ 1፥3ን ተመልከቱ፦ “ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ የመለኮቱ ኀይል ሰጥቶናል።”

በሕይወት ለመኖር እና መንፈሳዊ ለመሆን የሚያስፈልገው ኅይል ሁሉ በዕውቀት የሚገኝ ነው! የሚገርም ነው! ዶክትሪን እና የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዛትን ማስቀደም አለብን ማለት ነው! ሕይወታችን እና መንፈሳዊነታችን የተመሰረተው በዚህ ላይ ነው።

ማወቅ ብቻ መንፈሳዊነትን አያረጋግጥም። አለማወቅ ግን ከእውነተኛ መንፈሳዊነት ያጎድላል፣ ኀጢአታዊ ኑሮንም ያለማምዳል። ጴጥሮስ እንደሚለው ወደ መንፈሳዊነት የሚመራው መለኮታዊ ኅይል የሚገኘው እግዚአብሔርን በማወቅ ውስጥ ነው።

ሦስት አንድምታዎች፣ አንድ ማስጠንቀቂያ እና አንድ ምክር ከእግዚአብሔር ቃል ልስጣችሁ፦

  1. አንብቡ! አንብቡ! አንብቡ! ነገር ግን በማይረባ ሥነ-መለኮታዊ ገለባ ላይ ጊዜያችሁን አታጥፉ። ወደ ክብር እና ጸጋ ስለጠራችሁ ስለ እርሱ የሚያስተምሯችሁን በዶክትሪን የበለጸጉ መጽሐፍት አንብቡ።
  2. አሰላስሉ! አስላስሉ! ቀስ በሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስን ስታነቡ ምን ማለት እንደሆነ ለማሰብ ጊዜ ውሰዱ። ጥያቄዎችን ጠይቁ፣ ማስታወሻ ያዙ። ትሁት በሆነ መንፈስ ግራ የሚገቡ ነገሮችን ለመረዳት ሞክሩ። በእውነት ዛፍ ላይ ተጠላልፈው የበቀሉ የእውነት ቅርንጫፎችን ቀስ ብሎ በመፍታት ጥልቅ የሆነ መረዳት ይገኛል።
  3. ተወያዩ! ስለ እውነት ግድ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ውስጥ አባል ሁኑ። ማውራት እና ችግሮችን መፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ ለመጽሐፍ ቅዱሳዊ ችግሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ መፍትሔዎችን በመፈለግ የሚያምን ቡድን ውስጥ ተሳተፉ።

ማስጠንቀቂያ፦ “ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል” (ሆሴዕ 4፥6)፤ “ለእግዚአብሔር ቀናተኞች እንደሆኑ ስለ እነርሱ መመስከር እችላለሁና፤ ቅናታቸው ግን ከዕውቀት የተነሣ አይደለም” (ሮሜ 10፥2)። ስለዚህ ባለማወቅ ከሚመጡ ገዳይ ችግሮች ተጠንቀቁ።

በመጨረሻም፣ ምክር፦ “እግዚአብሔርን እንወቀው፤ የበለጠ እናውቀውም ዘንድ እንትጋ” (ሆሴዕ 6፥3)።