ክርስቶስ ይገባው ይሆን? | ግንቦት 24

“ወደ እኔ የሚመጣ ሁሉ አባቱንና እናቱን ሚስቱንና ልጆቹን፣ ወንድሞቹንና እኅቶቹን፣ የራሱንም ሕይወት እንኳ ሳይቀር ባይጠላ፣ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም፤ የራሱንም መስቀል ተሸክሞ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።” (ሉቃስ 14፥26-27)

ኢየሱስ ለክርስትና የሚከፈለውን አስከፊ የሆነ ዋጋ፣ ያለ አንዳች ፍርሃት እና ሃፍረት በቀጥታ ነግሮናል፦ ቤተሰብን መጥላት (ቁጥር 26)፤ መስቀሉን መሸከም (ቁጥር 27)፤ እና ያለንን ሁሉ መተው ነው (ቁጥር 33)። በዚህ የፀጋ ቃል ኪዳን መጽሐፍ ውስጥ በትንንሽ የተጻፈ፣ የማይታይ ነገር የለም። ሁሉም ነገር በትልልቁ ግልጽ ሆኖ ተጽፏል። ፀጋ ርካሽ አይደለም! ዋጋ ያስከፍላል! ጥሪውም “ኑ፣ ደቀ መዛሙርቴ ሁኑ” የሚል ነው።

ሰይጣን ግን በተቃራኒው የራሱን አስከፊዎቹን እውነታዎች ደብቆ መልካም የሚመስሉትን ብቻ ያሳያል። በሰይጣን መጽሐፍ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ዘግናኝ ነገሮች፣ እንዳይነበቡ ሲባል በጥቃቅን ፊደላት ከጀርባ የተጻፉ ናቸው።

ለምሳሌ ከፊት ባለው ገፅ ላይ ስታነቡ የምታገኙት፣ “መሞት እንኳ አትሞቱም” (ዘፍጥረት 3፥4) የሚለውና፣ “ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ እሰጥሃለሁ” የሚሉትን ቃላት ነው (ማቴዎስ 4፥9)። ነገር ግን ከጀርባ ባለው ገፅ ላይ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ መነጽር ካልሆነ በቀር በማይታዩ ጥቃቅን ፊደላት የተጻፈው እንዲህ ይላል፦ “ከዚህ ሁሉ ጊዜያዊ ደስታ በኋላ፣ ከእኔ ጋር በሲዖል አብራቸሁ ትሰቃያላችሁ።” ይሄን ግን አይነግሯችሁም።

ለምንድን ነው ሰይጣን መልካሙን ብቻ በማሳየት ሲዋሽ፣ ኢየሱስ ከባዱንም ጥሩውንም ሊያሳየን የፈቀደው? በበርካታ ክርስቲያኖች ዘንድ እውቅ የሆነው ኢንግሊዛዊው ጸሐፊ ማቲው ሄንሪ እንዲህ ሲል ይህን ጥያቄ ይመልሳል፦ “ሰይጣን መጥፎውን ደብቆ መልካሙን ብቻ የሚያሳየን፣ የእርሱ መልካም ከመጥፎው ጋር ፈፅሞ ስለማይመጣጠን ነው — ክፋቱ እጅግ ያይላል። የክርስቶስ መልካም ግን የትኛውንም መጥፎ ወይም ክፉ ነገር በብዙ እጥፍ ያሸንፋል።”

የኢየሱስ ጥሪ ሙሉ በሙሉ የመከራ እና ራስን የመካድ ጥሪ ብቻ አይደለም። እንዲያውም ከሁሉም በፊት፣ ወደ ታላቅ ድግስ ኑ የሚል የግብዣ ጥሪ ነው። በሉቃስ 14፥16-24 ያለው ምሳሌ ዋና መልዕክቱ ይህ ነው። ከዚያ ደግሞ፣ ኢየሱስ ሁሉንም መከራ እና እጦት የሚክስበትን ዳግም ትንሳዔን ቃል ይገባል (ሉቃስ 14፥14)። በመከራዎች ውስጥ እንደሚያግዘንም ይነግረናል (ሉቃስ 22፥32)። አባታችን እግዚአብሔር ደግሞ መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጠንም ይነግረናል (ሉቃስ 11፥13)። እንደው ለመንግሥቱ ብንሞት እንኳ ከራሳችን ጠጉር አንድ እንኳ እንደማትጠፋ ቃል ይገባልናል (ሉቃስ 21፥18)።

ስለዚህ ቁጭ ብለን ክርስቶስን የመከተል ዋጋውን ስናሰላው፣ ጥሩውን ከከባዱ ስንመዝነው፣ ሽልማቱን ከመከራው ስናወዳድረው፣ እውነትም ይገባዋል። ከበቂ በላይ ይገባዋል (ሮሜ 8፥182 ቆሮንቶስ 4፥17)።

ለሰይጣን ግን እንዲህ እንለዋለን፦ “ሰው በማጭበርበር ያገኘው ምግብ ይጣፍጠዋል፤ በመጨረሻ ግን አፉን ኰረት ሞልቶት ያገኘዋል” (ምሳሌ 20፥17)።