የእግዚአብሔር ፍቅር በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ነውን? | ሕዳር 1

ነገር ግን ጸጋን አብዝቶ ይሰጠናል፤ መጽሐፍም፣ “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ያለው ስለዚህ ነው። እንግዲህ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አስገዙ፤ ዲያብሎስን ተቃወሙት፤ ከእናንተም ይሸሻል። ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል። (ያዕቆብ 4፥6–8)

ያዕቆብ “የተትረፈረፈ ጸጋ” እና እግዚአብሔር “ወደ እኛ የሚጠጋበት” ጣፋጭ የህይወት ልምምዶች እንዳሉ ያስተምረናል። በርግጥም እግዚአብሔር ወደ እኛ መቅረቡ እና የተትረፈረፈ ጸጋ ማግኘትን መለማመዳችን አስደናቂ ነገር ነው። ታዲያ ይህን የእግዚአብሔር ፍቅር የምንለማመደው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ነው? አይደለም! ቅድመ ሁኔታዎች አሉ። ቅድመ ሁኔታውም የተመሠረተው ራሳችንን በማዋረዳችን እና ወደ እግዚአብሔር በመቅረባችን ላይ ነው። እግዚአብሔር “ለትሑታን ግን ጸጋን [አብዝቶ] ይሰጣል። … ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል።

ትዕቢትን እንድንዋጋ፣ ትህትናን እንድንፈልግና የእግዚአብሔርን መቅረብ ዋጋ እንድንሰጥ የሚጠይቁ ውድ የእግዚአብሔር ፍቅር ልምምዶች አሉ። ቅድመ ሁኔታዎቹም እነዚህ ናቸው። እርግጥ ነው፣ ቅድመ ሁኔታዎቹ በራሳቸው በእኛ ውስጥ ያሉ የእግዚአብሔር ሥራ ናቸው። ነገር ግን እኛም የምናሟላቸው ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው።

ይህ እውነት ከሆነ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ምንም ዐይነት ቅድመ ሁኔታ እንደሌለው የሚገልጹ፣ ብቁ ያልሆኑና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የሌላቸው ማረጋገጫዎች፣ ብዙ ሰዎች በጣም የሚጓጉለትን ሰላም መጽሐፍ ቅዱስ በሚያዝዘው በኩል እንዳያገኙ የሚጋርዱ ከንቱ ማረጋገጫዎች ናቸው ብዬ እፈራለሁ። ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የሚገኝን ሰላም ለመስጠት ስንሞክር፣ ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያዝዘው መድኃኒት እያራቅናቸው ሊሆን ይችላል።

አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር፣ በእግዚአብሔር ምርጫ፣ በክርስቶስ ሞት እና በአዲሱ ውልደታችን በኩል የተገለጠው መለኮታዊ ፍቅር ምንም ዐይነት ቅድመ ሁኔታ የሌለው ነጻ ስጦታ መሆኑን ነው። ይህንን እውነት በጩኸትና በጥራት ልናውጀው ይገባል።

በተጨማሪም፤ መጽደቃችን በእኛ መታዘዝ ላይ የተመሠረተ ሳይሆን፣ በክርስቶስ መታዘዝና መሥዋዕትነት ላይ የተመሰረተ የመሆኑን የምሥራች ሳንታክት ልንሰብክ ይገባናል። ቃሉ እንደሚል፦ “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ” (ሮሜ 5፥19)።

ነገር ግን፣ ሙሉ እና ጣፋጭ የሆነውን የእግዚአብሔር ጸጋ እና መገኘቱን በቅርበት እየተለማመዱ ማጣጣም የሚችሉት፣ በየቀኑ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደረጉ እና ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ሰዎች እንደሆኑ የሚናገረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነትንም አብረን እናውጅ።