ጽናታችሁ የተገዛው በኢየሱስ ነው | ነሐሴ 6

“ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ የሚመሠረት አዲስ ኪዳን ነው” (ሉቃስ 22፥20)

ይህ ማለት በኤርሚያስ 31 እና 32 ላይ በግልጽ የተሰጠውን የአዲሱ ኪዳን ተስፋ፣ በኢየሱስ ደም እርግጠኛ ሆኗል ወይም ታትሟል ማለት ነው። መሲሑን ለሚያምኑት የእግዚአብሔር ሕዝቦች አዲሱ ኪዳን እውን ሆኗል፤ ኢየሱስም የሞተው ያንን ለመመሥረት ነው።

አዲሱ ኪዳን የክርስቶስ ለሆኑት ሁሉ ምን ያስገኝላቸዋል ለሚለው ጥያቄ መልሱ፣ እስከ መጨረሻው በእምነት መጽናትን ያስገኝላቸዋል የሚል ነው።

ኤርምያስ 32፥40ን አድምጡ፦

“መልካምን ነገር ለእነርሱ ከማድረግ እንዳልቈጠብና ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።”

አዲሱ እና የዘላለሙ ኪዳን ሊሻር የማይችለውን ይህን ተስፋ ይዟል፤ “ ከእኔም ፈቀቅ እንዳይሉ መፈራቴን በውስጣቸው ላኖር ከእነርሱ ጋር የዘላለም ቃል ኪዳን እገባለሁ።” ፈቀቅ ሊሉ አይችሉም። አይሉም። ይህንን ኪዳን ክርስቶስ በደሙ አትሞታል። በእምነት በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ ከሆናችሁ መጽናታችሁን እርሱ በደሙ ገዝቶታል።

ዛሬ በእምነት እየጸናችሁ ከሆነ፣ የመጽናታችሁ ምክንያት የኢየሱስ ደም ነው። በውስጣችሁ እየሰራ ያለው መንፈስ ቅዱስ እምነታችሁን በማጽናት ሲተጋ፣ ኢየሱስ በደሙ የገዛውን እያከበረ ነው። እግዚአብሔር ወልድ ለእኛ ያስገኘልንን እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ይሠራዋል። አብ አቀደው። ኢየሱስ ገዛው። መንፈስ ቅዱስ ፈጸመው። እያንዳንዳቸው ያለ አንዳች ስሕተት – እስከፍጻሜው።

እግዚአብሔር በደም ዋጋ ለተገዙት ልጆቹ ጽናት እና ዘላለማዊ ድነት ሙሉ ለሙሉ ቁርጠኛ ነው።