ኢየሱስ የሞተው ለዚህ ነው | መጋቢት 20

ከክርስቶስ ጋር ተሰቅያለሁ፤ ከእንግዲህ እኔ አልኖርም፤ ነገር ግን ክርስቶስ በውስጤ ይኖራል። አሁንም በሥጋ የምኖረው ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት ነው (ገላትያ 2፥20)።

ዛሬ ጠዋት ከእንቅልፌ ስነቃ ለጥቂት ሰከንዶች በአዕምሮዬ አንድ ዐሳብ ብልጭ አለ። ሞቼ፣ በቅዱሱ እግዚአብሔር ፊት ብቻዬን ባዶ ሕይወቴን ይዤ፣ ያለ ምንም አማላጅ ወይም ደጋፊ ስለመቆም አሰብኩ።

በቅጽበት ከባድ የሆነ ድንጋጤ እና ጭንቀት ወረረኝ። ወዲያውኑም ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ልክ ለዚህ ዐይነት ጊዜ መሆኑ ብልጭ አለልኝ። ከዚያም ያ ከባድ ስሜት ጠፋ።

በቅድሚያ የተረዳሁት አንድ ነገር ይህ ነው። በትክክል የዳነ አንድ ሰው የሚሰማው ስሜት ይህ ነው ብዬ አሰብኩ። ኢየሱስ ክርስቶስ እውነት መሆኑን ውስጣችን የሚረዳው በዚህ አስደንጋጭ ስሜት ነው። የክርስቶስ ፍቅር የሚበራልን ይሄን ጊዜ ነው። ድንገት፣ በሆነ ቅጽበት፣ ከነ ቆሻሻ ሕሊናችን እና ወንጀለኛ ማንነታችን በቅዱሱ እግዚአብሔር ፊት መቆማችን የማይቀር መሆኑን ስናስብ በድንጋጤ ክው የምንልባት ቅጽበት ታስፈልጋለች።

የዚህ ስሜት ተፅዕኖ ከባድ ነው። ያለ አማላጅ ተስፋ እንደሌለን እንመለከታለን። ብቻችንን የቆምን፣ ተስፋ የሌለን፣ ኅጢአተኛ ሕይወታችንን ብቻ ይዘን የምንጠፋ ምስኪኖች ነን። በዚህ ቅዱስ አምላክ ፊት የዘላለም ሕይወት ሊሰጠን የሚችል አንዳች ጭላንጭል ተስፋ እንኳ ቢኖር፣ በራሳችን በፍጹም አንወጣውም። አዳኝ የሚሆን፣ ምትክ የሚሆን፣ ቤዛ የሚሆን ያስፈልገናል።

ታዲያ በዚህ አስጨናቂ ወቅት እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ምን የሚያስደስት ነገር አለ – “በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን አሳልፎ በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለኝ እምነት” መኖርን የመሰለ የት ይገኛል? (ገላትያ 2፥20)። ለሽራፊ ሰከንዶች፣ ጌታዬ በምትኬ ሳይቆም ቢቀር ኖሮ፣ የምዋጥበትን ጨለማ እና ፍርድ አስፈሪነት የማሰብ እድል አግኝቻለሁ። እንደው ለማሰብ ያክል፣ ወይ ለሥነ መለኮታዊ ክርክር የሚሆን ሳይሆን፣ የምር የገሃነም ደጃፍ ላይ ቆሜ ወደ ውስጥ የተመለከትኩ ያክል እስኪሰማኝ ድረስ፣ እርግጠኛ የሆነ ስሜት እና እውቀት ነው።

አምላካችን በእርግጥ የሚባላ እሳት ነው፤ ክፋትን በፍጹም አይታገስም። አዳኛችን ጣልቃ ባይገባ ኖሮ፣ በቁጣው ንዳድ ጠፍተን ነበር። አንዳች ማመካኛ ማቅረብ የማይቻልበት ተስፋ አስቆራጭ ችሎት ፊት ቆሜ ፍርዴን መጠበቅ። በዚህ ቅጽበት ጣልቃ ሊገባ የሚችለው ኢየሱስ ብቻ ነው! ኢየሱስ ብቻ! ኦ ኢየሱስ! ምስጋናዬን እንዴት ልግለጽልህ? ያመለጥኩትን መዓት፣ ያገኘሁትን ሕይወት እያሰብኩኝ የደስታውን ማዕበል ልቤ እንዴት ይግታው? ብቸኛ የምታስፈልገኝ የእግዚአብሔር ስጦታዬ፣ ስምህ ለዘለዓለም ይክበር!