ኢየሱስም ደቀ መዛሙርቱ ወዳሉበት ቀርቦ እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ሂዱና ሕዝቦችን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው፤ እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴዎስ 28፥18-20)።
የማቴዎስ ወንጌል የመጨረሻው ምዕራፍ ከሞት የተነሣውን ክርስቶስን ከነሙሉ ክብሩ የሚያሳየን መስኮት ነው። በዚያ ውስጥ የክርስቶስን ልዕልና የሚያሳዩ ቢያንስ ሦስት ታላላቅ ከፍታዎችን ታገኛላችሁ፦ የኀይሉን ከፍታ፣ የቸርነቱን ከፍታ እና የዓላማ ፈጻሚነቱን ከፍታ ነው።
ሥልጣን ሁሉ የእርሱ ነው፤ ይህ ማለት ፈቃዱን ለማድረግ መብቱም ሆነ ኀይሉም የእርሱ ነው። ይህን ኀይሉንም በመጠቀም፣ ከሁሉም ነገድ የተውጣጡ ደቀ መዛሙርትን የማፍራት ዓላማውን ያሳካል። በዚህ ሂደት ውስጥም ቸርነቱን ሊያበዛልንና እስከ መጨረሻውም ከእኛ ጋር አብሮን ሊሆን ቃል ገብቷል።
ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ታላቅነትን የማድነቅ ፍላጎታችንን በእርግጥም የሚያረካልን፣ በእርግጥም በሁሉ ነገር እጅግ ታላቅ ከሆነ ብቻ ነው። በኀይል ታላቅ። በቸርነት ታላቅ። በዓላማ ፈጻሚነት ታላቅ። ታላቅ እና ገናና።
ዓላማቸውን በማሳካት ደካማ የሆኑ ሰዎች ታላቅነትን የማድነቅ ፍላጎታችንን ሊያረኩልን አይችሉም። በሕይወታቸው ውስጥ ጭራሽ ዓላማ የሌላቸውን ሰዎች እንደማናደንቃቸው ግልጽ ነው። ከእነዚህ በባሰ ደግሞ ክፉ እና ራስ ተኮር የሆነ ዓላማ ያላቸውን ደግሞ ፈጽሞ አናደንቃቸውም።
ልናውቀው፣ ልናየው፣ እና ልንከተለው የምንናፍቀው ደካማ ያልሆነ፣ ለኀይሉ ገደብ የሌለው፣ ቸርና በርኅራኄ የተሞላ ደግሞም ጽኑና የማይነዋወጥ ዓላማ ያለውን ነው።
ደራሲዎች እና ገጣሚዎች፣ ተዋንያንና የፊልም ጸሐፊዎች አልፎ አልፎ በሥራዎቻቸው ወደዚህ ሰው ማንነት የሚጠጋጋ ጥላ ይፈጥራሉ። ነገር ግን የኤርታሌን ምስል በቴሌቪዥን መመልከት በአካል ሄዶ የመጎብኘት ጥማቴን እንደማያረካው ሁሉ፣ እነዚህም ጨረፍታዎች የአምልኮ ናፍቆታችንና ፍላጎታችንን ሊያረኩት አይችሉም።
እውነተኛው ነገር ያስፈልገናል። የኀይል፣ የቸርነት እና የቆራጥነት ሁሉ ጌታ የሆነውን ልናይ ጓጉተናል። ልናደንቅ እና ልናመልክ የተፈጠርነውም ሞትን ድል የነሳውን ይህንን ክርስቶስን ነው።