ባሎች ሆይ፤ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ፣ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ፣ እንዲሁም ጒድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው። (ኤፌሶን 5፥25-27)
በጋብቻ ውስጥ ብዙ ችግር የሚፈጠረው ባል እና ሚስት የራሳቸውን ደስታ ስለሚፈልጉ ሳይሆን፣ ደስታቸውን የትዳር አጋራቸውን ደስ በሚያሰኘው ነገር ውስጥ ስለማይፈልጉ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዝ ባልና ሚስት በአጋራቸው ደስታ ውስጥ የራሳቸውን ደስታ ይፈልጉ ዘንድ ነው።
ስለ ትዳር የሚናግረው ኤፌሶን 5፥25-30 በሰዎች ደስታ ውስጥ እንዴት እግዚአብሔር እንደሚከብር የሚናገር አስደናቂ ክፍል ነው። ባሎች ሚስቶቻቸውን ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደወደደ ሁሉ እንዲወዱ ተነግሯቸዋል።
እንዴት ነው ክርስቶስ ቤተክርስቲያንን የወደዳት? ቁጥር 25 “ራሱንም ስለ እርሷ አሳልፎ እንደ ሰጠ” ይላል፤ ግን ለምን? ቁጥር 26 “በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ በማንጻት እንድትቀደስ” ይላል፤ ይህን ማድረግ ለምን ይፈልጋል? ቁጥር 27 እንዲህ ሲል ይመልሳል፦ “ቅድስትና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን አድርጎ ለራሱ ሊያቀርባት ነው!”
“እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ” ሲል ምን ማለቱ ነው? የምን ደስታ (ዕብራውያን 12፥2)? ደስታው ሙሽራው ከሆነችው ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚፈጽመው ጋብቻው ነው። በደም በተገዛ ውብት አድምቆ ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ በማቅረብ ውስጥ ያለው ደስታ ነው።
ኢየሱስ የቆሸሸች እና ያልተቀደሰች ሙሽራ እንድትኖረው አይፈልግም። ስለዚህ ሊያነፃት፣ ቅድስት እና ነውር አልባ የሆነች ክብርት ቤተ ክርስቲያን ሊያደርጋት ለመሞት ፈቃደኛ ነበር። ለሙሽራው መልካም እንዲሆንላት ራሱን ለመከራ አሳልፎ በመስጠት የልቡን ፈቃድ አገኘ።
ጳውሎስ ይህንን በቁጥር 28-30 ወደ ባሎች ያመጣዋል፦ “ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል፤ ክርስቶስም ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው ልክ እንደዚሁ ነው፤ እኛ የክርስቶስ አካል ብልቶች ነንና።”
ኢየሱስ ለባልና ሚስቶች፣ ደግሞም ለሌሎች ሰዎችም “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል (ማቴዎስ 22፥39)። ጋብቻ ይህንን ትዕዛዝ ለመተግበር ልዩ ቦታ ነው። እንዲሁ ከላይ ከላይ “ራሳችሁን እንደምትወዱት” አይልም። አጥብቃችሁ ራሳችሁን እንደምትወዱት! እግዚአብሔር አንድ ሥጋ ያደረጋችሁን አጋራችሁን ስትወዱ ራሳችሁንም እየወደዳችሁ ነው። በትዳር አጋራችሁ ደስታ ውስጥ የራሳችሁን ደስታ የምታገኙት በዚህ መልክ ነው።