ኢየሱስ በጎቹን ይጠብቃል | ሐምሌ 23

ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “ስምዖን፣ ስምዖን ሆይ፤ እነሆ፣ ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ለመነ፤ እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ጸለይሁ፤ አንተም በተመለስህ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ።” (ሉቃስ 22፥​31–32)

ጴጥሮስ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ በመካዱ ቢወድቅም፣ ፈጽሞ እንዳይጠፋ የጠበቀው የኢየሱስ ጸሎት ነበር። ወደ መራራ ልቅሶና ንስሓ አምጥቶታል፤ በጴንጤቆስጤ ዕለት በነበረው መልእክቱ ውስጥ ወደታየው ደስታ እና ድፍረት አብቅቶታል። ኢየሱስ ዛሬም በተመሳሳይ መንገድ ስለ እኛ የሚማልደው እምነታችን እንዳይጠፋ ነው። ይህንን ደግሞ ጳውሎስ በሮሜ 8፥​34 ይናገራል።

ኢየሱስ፣ በጎቹ እንደሚጠበቁና በፍጹም እንደማይጠፉ ቃል ገብቷል። “በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ፤ እነርሱም ይከተሉኛል፤ እኔ የዘላለም ሕይወት እሰጣቸዋለሁ፤ ከቶ አይጠፉም፤ ከእጄም ሊነጥቃቸው የሚችል ማንም የለም” (ዮሐንስ 10፥27–28)።

ይህ የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር የበጎችን እምነት ለመጠበቅ ስለሚሠራ ነው። “በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እርሱ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ ቀን ድረስ ከፍጻሜው እንደሚያደርሰው ርግጠኛ ነኝ” (ፊልጵስዩስ 1፥6)።

የእምነትን ገድል ለብቻችን እንድንጋደል ለራሳችን አልተተውንም፤ “እንደ በጎ ፈቃዱ መፈለግንና ማድረግን በእናንተ ውስጥ የሚሠራ እግዚአብሔር ነውና” (ፊልጵስዩስ 2፥13)።

ልጆቹ ከሆናችሁ፣ “ፈቃዱን እንድታደርጉ በመልካም ነገር ሁሉ” ሊያስታጥቃችሁ እና “ደስ የሚያሰኘውንም በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል” ሊሰራባችሁ የእግዚአብሔር ቃል ማረጋገጫ አላችሁ (ዕብራውያን 13፥21)።

በእምነት እና በደስታ የመጽናታችን ጉዳይ በዋነኝነት ያለው በእግዚአብሔር እጅ ነው። አዎ መጋደል አለብን፤ ነገር ግን ይህ ተጋድሎ እግዚአብሔር በእኛ ውስጥ የሚሠራው ነው። በሮሜ 8፥30 ላይ “ያጸደቃቸውን እነዚህን ደግሞ አከበራቸው” እንደሚል በርግጥም እንዲሁ ያደርጋል። እግዚአብሔር ያጸደቃቸውን ልጆቹን በእርግጥም ያለምንም ጥርጥር በመጨረሻው ቀን ያከብራቸዋል። መክበራቸው እንደተፈጸመ ይቆጠራል።

ወደ እምነት ያመጣቸውን እና ያጸደቃቸውን አንዳቸውንም አይጥልም፤ እንዲጠፉ አይፈቅድም፤ ሁሉንም እስከመጨረሻው ይጠብቃቸዋል፣ ያድናቸውማል።