በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ፤ እኔ ዐውቃቸዋለሁ። (ዮሐንስ 10፥27)
“ኢየሱስ የእርሱ የሆኑትን ያውቃል” ይላል። ምንድን ነው የሚያውቀው?
ዮሐንስ 10፥3 እና ዮሐንስ 10፥27 ተቀራራቢ ናቸው። ቁጥር 3 እንዲህ ይላል፦ “በጎቹም ድምፁን ይሰማሉ። የራሱንም በጎች በየስማቸው እየጠራ ያወጣቸዋል።”
ስለዚህ፣ ኢየሱስ “ዐውቃቸዋለሁ” ሲል፣ ቢያንስ በስማቸው ያውቃቸዋል። እያንዳንዳቸውን በግልና በቅርበት ያውቃቸዋል ማለት ነው። በመንጋው ውስጥ ስማቸው የማይታወቅ ወይም የጠፉ በጎች የሉትም።
ዮሐንስ 10፥14-15 ደግሞ ሌላ ምልከታን ያሳየናል፦ “መልካም እረኛ እኔ ነኝ፤ በጎቼን ዐውቃለሁ፤ እነርሱም ያውቁኛል፤ ይህም አብ እኔን እንደሚያውቀኝ እኔም አብን እንደማውቀው ነው።”
ኢየሱስ በሰማይ ያለውን አባቱን የሚያውቅበት መንገድና በጎቹን የሚያውቅበት መንገድ ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ ራሱን በአብ ውስጥ እንደሚያየው ሁሉ፣ በደቀ-መዛሙርቱ ውስጥም ያያል።
ኢየሱስ የራሱን ባህርይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን በደቀ-መዛሙርቱ ውስጥ ይመለከታል። የእርሱ ምልክት በግንባራቸው ላይ አለ። ይህ ደግሞ በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ያደርጋቸዋል።
ሚስቱን በአየር መንገድ ማረፊያ ሆኖ እንደሚጠብቅ ባል፣ ሌሎች ሲወርዱ ዝም ብሎ ይመለከታል። በመጨረሻም ሚስቱን ሲያያት ይለያታል፣ ሁሉ ነገሯን ያውቀዋል፣ በዐይኖቿ ውስጥም የፍቅሩን የደስታ ነጸብራቅ ይመለከታል። በእርሷም ደስ ይለዋል። የሚያቅፈው እርሷን ብቻ ነው።
ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያስቀምጠዋል፦ “‘ጌታ የእርሱ የሆኑትን ያውቃል’ … የሚል ማኅተም ያለበት የማይነቃነቅ የእግዚአብሔር መሠረት ቆሟል” (2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥19)።
በእግዚአብሔር ልጅ በግል መታወቃችንና በልዩ ቁርኝት መወደደዳችንን ደግመን፣ ደጋግመን ብናወራው በዛ ሊባል አይችልም። ይህንን የመሰለ መታደል የለም። ይህ ለራሱ በጎች ብቻ የሰጠው፣ በግል አብሮነት ላይ የተመሰረተ፣ በልዩ ፍቅር የታተመ፣ የዘላለም ሕይወት ስጦታ ነው።