ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁል ጊዜ በሕይወት ስለሚኖር፣ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። (ዕብራውያን 7፥25)
ክርስቶስ ስለ እኛ ሁል ጊዜ እየማለደ ስለሚኖር፣ ለዘላለም እስከ ፍጻሜው ማዳን እንደሚችል ይናገራል። በሌላ አነጋገር፣ ስለ እኛ ለዘላለም የማይማልድ ከሆነ ለዘላለም ሊያድነን አይችልም ነበር።
ይህ ማለት፣ የክርስቶስ ክህነት የማይፈርስ እንደሆነ ሁሉ የእኛም መዳን የተጠበቀ ነው ማለት ነው። ተራ ስጋ ለባሽ ከሆነ ካህን እጅግ የሚበልጥ ካህን ያስፈልገን የነበረው ለዚህ ነው። የክርስቶስ አምላክነትና ከሙታን መነሣቱ፣ የማይሻረውን ክህነት አረጋግጦልናል።
ይህም ማለት ብዙ ጊዜ እንደምናወራው፣ ድነታችንን እንደ አንድ ወቅታዊ ክስተት ልናስበው አይገባም። “አንድ ጊዜ ጌታን ለመቀበል ወሰንኩ፣ ክርስቶስ ደሞ የሆነ ወቅት ላይ ሞቶ ተነሥቷል፤ በቃ ከዚህ ያለፈ ነገር የለም” ልንል አይገባም። በእርግጥ ከዚህ ያለፈ ነገር አለ።
እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በሰማይ ባለው በኢየሱስ የዘላለም ምልጃ እየዳንኩ ነው። ኢየሱስ ስለ እኛ እየጸለየ ነው፤ ይህም ለደህንነታችን አስፈላጊ ነው።
በኢየሱስ የሊቀ ካህንነት ምልጃ እና በሰማይ ባለው ዘላለማዊ ጸሎቱ እስከ ለዘለዓለም እንድናለን (ሮሜ 8፥34)(1ኛ ዮሐንስ 2፥1)። እርሱ ስለ እኛ ያለ ማቋረጥ ይጸልያል፤ እንከን የሌለበት ጸሎቱም የተመሰረተው ፍጹም በሆነው መስዋዕቱ ላይ ስለሆነ ጸሎቱ ተቀባይነትን ያገኛል።