የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነውን ኢየሱስን እንመልከት፤ እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታግሦ፣ የመስቀሉንም ውርደት ንቆ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአል። (ዕብራውያን 12፥2)
የኢየሱስ ምሳሌ፣ ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም መርህን ይቃረን ይሆንን? ክርስቲያናዊ ሄዶኒዝም የሚያመለክተው ደስታ የሚገኝበት መንገድ ፍቅር መሆኑን ነው። አንድ ሰውም ፍቅርን ሲመርጥ በዚህ ምክንያት ብቻ መሆን አለበት። ይህ ካልሆነ ግን ታላቁን አምላክ የሚታዘዘው በማጉረምረም ሲሆን፣ የጸጋው መገለጫ ከመሆን ጎድሎ የተገባለትን ሽልማት አራክሶ ይኖራል።
ዕብራውያን 12፥2 ኢየሱስ ከዚህ መርህ ጋር እንደማይቃረን በግልጽ የሚናገር ይመስላል።
ኢየሱስ በታሪክ ውስጥ ታላቁን የፍቅር ሥራ መሠራት የቻለው፣ ትልቁን ደስታ ስለፈለገ ነው። ይህም ደስታ የተቤዡ ሕዝቦች ባሉበት ወደዚያ ወደ እግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ማለት ነው፦ “እርሱ በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታገሠ!”
ይህንን ሲናገር ጸሐፊው፣ ኢየሱስን በዕብራውያን 11 ካሉት ቅዱሳን ጋር እንደ ምሳሌ እየጠቀሰ ነው። ቅዱሳኑ እግዚአብሔር በሚሰጠው ደስታ እርግጠኞች ከመሆናቸው የተነሣ “በኀጢአት የሚገኝን ደስታ” ንቀው ከእግዚአብሔር ጋር አብረው ይሆኑ ዘንድ መከራን መቀበል መረጡ (ዕብራውያን 11፥25)።
ስለዚህ በጌቴሴማኒ የጨለማ ሰዓቶች ክርስቶስን ደግፈው ከያዙት ነገሮች መካከል፣ ከመስቀል በኋላ ያለው የደስታ ተስፋ ነበር ማለት እንችላለን። ይህ ግን የፍቅሩን ታላቅነት አያሳንሰውም፤ ምክንያቱም ይህ ተስፋ ያደረገው ደስታ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ያመጣል (ዕብራውያን 2፥10)። ደስታው ለእግዚአብሔር ክብር በሚሆነው በመቤዠታችን ላይ ነው። ደስታውን ከኢየሱስ ጋር እንካፈላለን፤ እግዚአብሔር ክብሩን ይወስዳል።