ኢየሱስ ተልእኮውን ይጨርሳል | መጋቢት 16

“ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24፥14)

ከዚህ በላይ አበረታች እና አነሣሽ የሆነ የኢየሱስን የተስፋ ቃል አላውቅም።

  • ወንጌሉ መሰበክ አለበት አይደለም።
  • ወንጌሉ ሊሰበክ ይችላል አይደለም።
  • ወንጌሉ ይሰበካል።

ይህ ታላቁ ተልዕኮ ወይም ታላቁ ትዕዛዝ አይደለም፤ ታላቁ እርግጠኝነት ልንለው እንችላለን።

ማን እንደዚህ ሊናገር ይችላል? እንደሚሳካ በምን ያውቃል? ቤተ ክርስቲያን የተልዕኮ ሥራዋን እንደማትወድቅ በምን ያውቃል?

መልሱ፦ የተልዕኮ አገልግሎት ጸጋ ልክ እንደ ዳግም መወለድ ጸጋ ሁሉ መቋቋም የማንችለው ነው። ክርስቶስ ሉዐላዊ ስለሆነ ዓለም አቀፍ አዋጆችን ማወጅ ይችላል። ወደ ፊቱን ስለፈጠረው፣ የተልዕኮዎቹን የወደ ፊት ስኬት ያውቃል። ሕዝቦች ሁሉ ይሰማሉ!

“ሕዝቦች” ማለት “አገራት” ማለት አይደለም። ብሉይ ኪዳን ስለ ሕዝቦች ሲያወራ እንደ ኢያቡሳውያን፣ ፌርዛውያን፣ ኤዊያዊን፣ አሞራውያን፣ ሞዐባውያን፣ ከነዓናውያን እና ፍልስጤማውያን ስላሉ ቡድኖች እያወራ ነው። “ሕዝቦች” የራሳቸው ቋንቋ እና ባህል ያላቸው ብሔሮች ናቸው። “አሕዛብ ሁላችሁ፤ እግዚአብሔርን አመስግኑት፤ ሕዝቦችም ሁሉ፤ በምስጋና ከፍ ከፍ አድርጉት!” (መዝሙር 117፥1)።

እንደ ሉዓላዊ የእግዚአብሔር ልጅ እና የቤተ ክርስቲያን ጌታ፣ ኢየሱስ ይህንን መለኮታዊ ሁኔታ መረጠና እንዲህ ሲል በእርግጠኝነት ተናገረ፦ “ለሕዝብ ሁሉ ምስክር እንዲሆን፣ ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል…” (ማቴዎስ 24፥14)።

የወንጌል ተልዕኮ እንደሚሳካ ሙሉ ለሙሉ እርግጥ ነው። ሊወድቅ አይችልም። ታዲያ በታላቅ እምነት ልንጸልይ፣ በሙሉ እምነት ልንሠራ እና በድል ልንንቀሳቀስ አይገባም?