ኢየሱስ ጠላቶቻችንን ሁሉ ይረጋግጣቸዋል | ነሐሴ 27

ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል (1ኛ ቆሮንቶስ 15፥24)

የክርስቶስ አገዛዝ እስከምን ድረስ ነው?

ቀጣዩ ቁጥር በ1ኛ ቆሮንቶስ 15፥25፦ “ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና” ይላል። ሁሉ የሚለው ቃል የአገዛዙን ስፋት ይነግረናል።

በቁጥር 24 ላይ ያለው ሁሉ የሚለውም ቃል እንዲሁ የአገዛዙን ስፋት ይነግረናል፦ “ከዚያም ግዛትን፣ ሥልጣንና ኀይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፣ ያን ጊዜ ፍጻሜ ይሆናል።”

ክርስቶስ ለክብሩ ጠላት የሆነ የማያሸንፈው ምንም ዐይነት በሽታ፣ ሱስ፣ አጋንንት፣ ክፉ ልምምድ፣ ውድቀት፣ ድካም፣ ንዴት፣ ነጭናጫነት፣ ትዕቢት፣ ራስን ማጠልሸት፣ ጥል፣ ቅናት፣ ጠማምነት፣ ስግብግብነትና ስንፍና የለም።

በዚያ ተስፋ ውስጥ ያለው ማበረታቻ ደግሞ፣ የእምነታችሁንና የቅድስናቸሁን ጠላት ለመዋጋት ራሳችሁን ስታዘጋጁ የምትዋጉት ብቻችሁን አለመሆናችሁ ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ አሁን በዚህ ዘመን ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እያስገዛ ነው። እያንዳንዱ አገዛዝ፣ ሥልጣንና ኀይል ሁሉ ይንበረከካል።

ስለዚህም፣ ክርስቶስ በአጽናፈ ዓለሙ ሁሉ ውስጥ የማይገዛበት አንድም ክልል የለም። የክብሩ ጠላት በሆነ በየትኛውም ትንሽ እና ገናና የሚባል ኀይል ሁሉ ላይ ይነግሳል። በሕይወታችሁ የተደነቀረ ማንኛውንም የክብሩ ጠላት ለዘለዓለም ይሸነፋል።