ያልተገደበ ደስታ | መስከረም 28

ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን፣ አንተን እንዲያውቁ አድርጌአለሁ፤ እንዲያውቁህም አደርጋለሁ” (ዮሐንስ 17፥26)።

ከላይ ያለው ጸሎት ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የጸለየው ነው። ፍጹም ባልተገደበ ኅይል እና ግለት ለዘላለም ሐሴትን ማድረግ ምን ሊመስል እንደሚችል አስቡት። ሆኖም አሁን ይህንን እየተለማመድነው አይደለም። በዚች ዓለም ውስጥ ሆነን ፍጹም እርካታን እንዳናገኝ ሦስት እክሎች በመንገዳችን ቆመዋል።

የመጀመሪያው፣ በዚህ ዓለም ውስጥ ትልቅ ዋጋ ኖሮት፣ የልብን ጥልቅ መሻት የሚሞላ አንዳችም ነገር የለም።

ሁለተኛ፣ የከበሩ ነገሮችን በዋጋቸው ልክ ለማጣጣም አቅሙ የለንም።

ፍጹም እርካታን እንዳናገኝ የቆመው ሦስተኛው እክል ደግሞ፣ እዚህ ያሉን ደስታዎች የሚያበቁ መሆናቸው ነው። ምንም ነገር ዘላቂ አይደለም። ሆኖም ግን በዮሐንስ 17፥26 ላይ ያለው የኢየሱስ አጀንዳ እና ጸሎት ከተፈጸመ፣ ነገሩ ሁሉ ይቀየራል፦ “ለእኔ ያለህ ፍቅር በእነርሱ እንዲሆን፣ እኔም በእነርሱ እንድሆን” ብሎ ጸልዩአል። እግዚአብሔር ለልጁ ያለውን ፍጹም ፍቅር፣ በእኛም ውስጥ ገልጦታል!

እግዚአብሔር በልጁ እንደተደሰተው እኛም በልጁ ከተደሰትን፣ እንግዲህ የደስታችን ማዕከል የሆነው ኢየሱስ የማያልቀው ትልቁ ሀብታችን ሆነ ማለት ነው። መቼም ቢሆን አይሰለቸንም፤ ልባችንን ሊሰብር አይችልም፤ ፈጽሞ አያስከፋንም።

ከእግዚአብሔር ልጅ በላይ ዋጋ ያለው ሀብት ሊገኝ አይችልም።

በዚህ የከበረ ሀብት ለመደሰት፣ አቅማችን በሰዋዊ ድክመቶች አይገደብም። አብ በልጁ እንደተደሰተው እኛም በልጁ እንደሰታለን። ኢየሱስ የጸለየው ይህ እንዲሆን ነው!

እግዚአብሔር በልጁ ያለው ደስታ በእኛም ውስጥ ይኖራል፤ እኛም በልጁ እንደሰታለን። ይህ መቼም አያበቃም፤ ምክንያቱም አብም ወልድም ዘላለማዊ ናቸው።

እነርሱ በሚዋደዱበት ፍቅር፣ እኛም እንወዳቸዋለን። ከዚህ የተነሣ ለእነርሱ ያለን ፍቅር ምንጊዜም አያረጅም፤ ደግሞም አይጠፋም።