ፍትሕ ይፈጸማል | መስከረም 29

ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቊጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ ‘በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ’ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና” (ሮሜ 12፥19)።

ሁላችሁም በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ተጎድታችኋል። ምናልባትም አብዛኞቻችሁ አንድም ጊዜ ይቅርታ ባልጠየቀ ወይም ነገሩን ለማቅናት ተገቢውን ጥረት ባላደረገ ሰው ተጎድታችኋል።

መራርነቱን እና ሕመሙን እንዳትተዉት ከሚያደርጓችሁ ነገሮች አንዱ፣ ፍትሕ መስፈን አለበት የሚለው ምክንያታዊ አቋማችሁ ነው። ሰዎች ክፋትን አድርገው፣ ለመሰሪነታቸው የማይጠየቁ ከሆነ፣ መላ ዓለሙ የተጋመደበት የሞራል (እሴት) ገመድ ይበጠሳል የሚል አቋም ስላላቸሁ ነው።

ይህ የፍትሕ ጥያቄ፣ ይቅር እንዳንልና ቂም እንድንይዝ ከሚያደርጉን ምክንያቶች አንዱ ነው። ብቸኛው ግን አይደለም። ሁላችንም የራሳችን ኅጢአቶች አሉብን።

ጉዳዩን ብንተወው፣ ፍትሕ ያልተገኘ መስሎ ስለሚታየን መተው አንችልም።

ታዲያ ንዴታችንን ይዘን እንብሰለሰላለን፦ “ይህ ሊሆን አይገባም! በድሎኛል! እንዴት እኔ እየተቃጠልኩ እርሱ ደስተኛ ይሆናል? አስቀይሞኛል! በጣም አስቀይሞኛል” እንላለን። ምሬታችን ደግሞ ሁሉንም ነገር መበከል ይጀምራል።

ሮሜ 12፥19 ላይ ያለው ቃል የተሰጠን፣ ይህን ሸክም ከላያችን ላይ ለማንሣት ነው።

“ለእግዚአብሔር ቊጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ።” ይህ ለእናንተ ምን ማለት ነው?

ንዴታችሁን ትታችኋል፣ የተጎዳችሁበትን ነገር ትታችኋል፣ ምንም ነገር አልደረሰባችሁም ማለት አይደለም። ደርሶባችኋል።

ፍትሕ የለም ማለትም አይደለም። ቀን አይወጣላችሁም ማለትም አይደለም። ያለ ምንም ቅጣት በዳዮቻችሁ አምልጠዋል ማለትም አይደለም። አላመለጡም።

የበቀልን ሸክም ስታስቀምጡት፣ እግዚአብሔር ያነሣዋል ማለት ነው

ይህ በሌላ መንገድ በቀል የማግኛ መንገድ ሳይሆን፣ በቀልን የእኔ ነው ላለው ለእግዚአብሔር መስጠት ነው። “በቀል የእኔ ነው” ይላል እግዚአብሔር። “እናንተ አስቀምጡት እኔ አነሣዋለው፤ ፍትሕም ይፈጸማል።” እንዴት ያለ ታላቅ እረፍት ነው። ይህንን ሸክም መሸከም የለብኝም። ለረዥም ጊዜ እፎይ ብሎ እንደመተንፈስ ነው። በተጨማሪም ለመውደድ ነፃ እንደመሆን ነው።